የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ተቋርጦ የቆየው ውድድር በአራት ጨዋታዎች ተመልሷል

ለኢንተርናሽናል ውድድሮች ዝግጅት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሲጀምር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ድል አድርገዋል።

ረፋድ ላይ በጀመረው በመጀመሪያ መርሃግብር ንግድ ባንክ ከመቻል ጋር ተገናኝተው ኢትዮ ንግድ ባንክ ነገ የሚደረጉ ጨዋታዎችን እየጠበቀ የሊጉ መሪ መሆን የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል። በመጀመሪያ አጋማሽ ፍፁም የጨዋታ በላይነት በመውሰድ የተጫወቱት ንግድ ባንኮች ገና ጨዋታው ከመጀመሩ ነበር የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት።

የሙከራቸው ጥረት ተሳክቶ በ13ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ ቅብብል የተገኘውን ኳስ የፊት መስመር ተጫዋች የሆንችው ሴናፍ ዋቁማ በቀድሞ ክለቧ ላይ ግብ አስቆጥራ ንግድ ባንክ መሪ ማድረግ ችላለች።በዚህ ብቻ ያላበቁት ንግድ ባንኮች በ21ኛው ደቂቃ ሰናይት ቦጋለ ከግብ ክልል ውጭ ሆና አክርራ መታ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር መሪነታቸውን ሁለት አድርጋለች።

በአንደኛ አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉት መቻሎች እምብዛም የግብ ሙከራ ሲያድርጉ አልተስተዋሉም። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አለመረጋጋት ተስኗቸዋል። ተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የተሰተዋሉት ንግድ ባንኮች በ25ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ ያገኙትን መሳይ ተመስገን ቀጥታ ወደ ግብ መጥታ አስቆጥራ ሶስት ለምንም እየመሩ እረፍት እንዲወጡ አድርጋለች።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ብዙ ግቦች ያልተቆጠሩበት እንዲሁም አስቆጪ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ሁለተኛ አጋማሽ ለመመልከት ችለናል። ሆኖም ግን ጨዋታው ሊጠናቀቅ አከባቢ መቻሎች ግቦችን ለማስቆጠር ወደፊት ገፍተው ተጫውተዋል። በ85ኛው ደቂቃ በግብ ክልል አከባቢ በተፈጠረ ንክኪ መቻሎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ምንትዋብ ዮሐንስ ከሽንፈት ያልታደገቻቸውን ግብ አስቆጥራ ጨዋታው 3ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በማስከተል በተደረገው መርሃግብር አርባምንጭ ከተማ በጠባብ ውጤት አዲስአበባ ከተማን አሸንፏል።

ጥሩ ፋክክር በሳየው በ5 ሰዓቱ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ይዘው ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ አድርገዋል ፤ እንዲሁም በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ሲያድርጉ ተስተውሏል። አርባምንጭ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም። አዲስ አበባ ከተማም በአንፃሩ በጥሩ ኳስ ቁጥጥር ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክፍል በመሄድ ሙከራ አድርገዋል። ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ እረፍት ለመውጣት ተገደዋል።

 

ከመልበሻ ክፍል መልስ የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ይዘው የገቡት አዞዎቹ በ56ኛው ደቂቃ ፎዚያ መሐመድ በራሷ ጥረት ኳስን ይዛ ገብታ ከመረብ ጋር አገናኝታ ቀዳሚ እንዲሆኑ አድርጋለች። በተጨማሪም አዞዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እስከመጨረሻው ደቂቃ ሲታገሉ ተስተውለዋል።

አዲስ አበባ ከተማዎችም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲገቡ ለማየት ተችሏል። ሆኖም ግን ጠንከራ ሆኖ የዋለውን የአዞዎቹን ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ጨዋታውም በፎዚያ መሐመድ ብቸኛ ግብ በአዞዎቹ በላይነት ተገባዷል።

ቀን 8:00 ሰዓት ድሬዳዋ ከተማን ከይርጋጨፌ ቡና ያገኘው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃዎች ባስቆጠሩት ግብ ድሬዎች ድል ተቀናጅተዋል።

ብዙም የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት በዚህ ጨዋታ ቀዝቀዝ ያለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለመመልከት ችለናል። ሁለቱም ቡድኖች በአንደኛው አጋማሽ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን ለግብ የተቃረበ ሙከራ እንኳን ሲያድርጉ አልተስተዋሉም። በዚህም ያለምንም የግብ ሙከራ ወደመልበሻ ክፍል ተመልሰዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ያደረጉት ድሬዎች በኳስ ቁጥጥር የተሳካ የሚባል ሁለተኛ አጋማሽ ማሳለፍ ችለዋል። ከብዙ ከግብ ሙከራ በኋላ በ85ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ አግኝተው ሰርከአዲስ ጉታ ወደግብ መትታ ወደግብነት ቀይራ ድሬዎች ድል እንዲጎናፅፉ አድርጋለች።

የዕለቱ በመጨረሻ ጨዋታ አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ተገናኝተው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ጥሩ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ጠንከር ያለ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ የጨዋታ ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ሲያድርጉ ተስተውለዋል። በሁለቱም ቡድኖች መካከል ብዙ የግብ ሙከራዎች ከተደረጉ በኋላ በ25ኛው ደቂቃ ምትኬ ብርሃኑ በእራሷ ጥረት በርቀት አክሪራ መጥታ ባስቆጠረችው ግብ ሲዳማ ቡና መሪ መሆን ችሏል።

ሆኖም ግን በመሪነት የቆዩት ለሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር። በ27ኛው ደቂቃ የአዳማ ከተማዋ የፊት መስመር ተጫዋች ሔለን እሸቱ ከግብ ክልል ውጪ ሆና ወደ ግብ የመታችው ኳስ የሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ በቀላሉ ለመያዝ ሲትሞክር አምልጧት ወደግብነት ተቀይሮ አቻ እንዲሆኑ ሆኗል።

በሁለተኛው አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ፉክክር ያስመለከቱ ሲሆን በርከት ያሉ ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን ሲያድርጉ መመልከት ትችሏል። በተለይም ጨዋታው ሊጠናቀቅ አከባቢ ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ በማጥቃት ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በዚህም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።