ሪፖርት | መቻል የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት አጠናቋል

በምሽቱ ጨዋታ መቻሎች በከነዓን ማርክነህ ግብ ሻሸመኔን 1ለ0 በመርታት የመጀመሪያውን ዙር በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሆነው ጨርሰዋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሻሸመኔ ከተማ እና መቻል ሲገናኙ ሻሸመኔዎች በ14ኛው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ኢዮብ ገብረማርያም በአሸናፊ ጥሩነህ ተተክቶ ሲገባ መቻሎች በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 4ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ምንተስኖት አዳነ ፣ ፍጹም ዓለሙ ፣ አቤል ነጋሽ እና ቺጂኦኬ ናምዲ በግርማ ዲሳሳ ፣ ዮሐንስ መንግሥቱ ፣ ምንይሉ ወንድሙ እና በረከት ደስታ ተተክተው ገብተዋል።

12፡00 ሲል በዋና ዳኛ መለሠ ንጉሤ መሪነት መጠነኛ ፉክክር እየተደረበት በተጀመረው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች 14ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሽመልስ በቀለ ከተጋጣሚ ቡድን የቀማውን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሮት ቺጂኦኬ ናምዲን ገጭቶ ሲመለስ ኳሱን ያገኘው ከነዓን ማርክነህ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ በግሩም አጨራረስ በግቡ የግራ ክፍል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

መቻሎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ ሲሞክሩ 21ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ቺጂኦኬ ናምዲ አኩኔቶ በግንባሩ ገጭቶ ግሩም ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ የነበር በመሆኑ ግቡ ሲሻር ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ከነዓን ማርክነህ ከስቴፈን ባዱ አኖርኬ ከቀኝ መስመር በእጅ በተወረወረ እና በቺጂኦኬ ናምዲ በተመቻቸ ኳስ ጥሩ የግብ አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ መሻሻል እያሳዩ የሄዱት ሻሸመኔዎች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የተደራጀ እና ፈታኝ የሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ 25ኛው ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ ከቅጣት ምት ያደረገው በግቡ የግራ ቋሚ ዒላማውን ሳይጠብቅ የወጣው ሙከራ የተሻለው ሙከራቸው ነበር። ሆኖም ግን 34ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው እጅግ ተቃርበው ፍጹም ዓለሙ ከግራ መስመር በድንቅ ዕይታ ያሸጋገረውን ኳስ ቺጂኦኬ ናምዲ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ በግሩም ሁኔታ ቢመታውም የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረገው ፍልሚያ ውጪ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም ነበር። ሆኖም 55ኛው ደቂቃ ላይ በመቻል በኩል ሽመልስ በቀለ ከፍጹም ዓለሙ ጋር ጥሩ ቅብብል አድርጎ ግብ ጠባቂውን አታልሎ በማለፍ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያሻማውን ኳስ የሻሸመኔው የመሃል ተከላካይ የአብሥራ ሙሉጌታ በግንባር በመግጨት አስወጥቶታል።

ደካማ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ መቻሎች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ማሰኬድ ሲችሉ 65ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ከነዓን ማርክነህ ወደ ሳጥን እየገፋ በመግባት የአብሥራ ሙሉጌታን አታልሎ በማለፍ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በሻሸመኔዎች በኩል ደግሞ 69ኛው ደቂቃ ላይ ጌትነት ተስፋየ ከረጅም ርቀት ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መጠነኛ ፉክክር ሲደረግ በመቻል በኩል 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው በረከት ደስታ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) በጭማሪ ደቂቃ ውስጥም ከነዓን ማርክነህ በተከላካዩ የአብሥራ ሙሉጌታ ስህተት ባገኘው ኳስ ካደረጉት ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይኖር ጨዋታው በመቻል 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም መቻል በ33 ነጥቦች የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጦ የውድድር ዘመኑን አጋምሷል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔው አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ ግብ ያስተናገዱበት መንገድ በራሳቸው ስህተት እንደነበር ሆኖም ግን ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው እንደቀረቡ ሲጠቁሙ ዳኝነቱ ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው በመናገር የተጫዋቾች ምልመላ ላይ ክፍተት እንደነበር ሀሳባቸውን ሲሰጡ የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠራቸውን እና በእንቅስቃሴውም ደስተኛ እንደሆኑ ሲናገሩ በመጀመሪያው ዙር 30 ነጥብ የማምጣት ዕቅድ ይዘው ያንም እንዳሳኩ በመጠቆም ለሁለተኛው ዙር ውድድር የሚያርሙት እንቅስቃሴ ቢኖርም በቂ ጊዜ እንደሌለ እና ተጫዋቾችም ዕረፍት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ አወዳዳሪው አካል መርሐግብሩ ላይ ቢያስብበት ብለዋል።