ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

የጣና ሞገዶቹ በቸርነት ጉግሳ ብቸኛ ግብ የጦና ንቦችን በማሸነፍ የመጀመርያውን ዙር አገባደዋል።

ወላይታ ድቻዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከተለያየው አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ ባህር ዳር ከተማዎች ግን ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ካስተናገደ ስብስብ አላዛር ማርቆስ ፣ ፍራወል መንግሥቱ እና ፍፁም ጥላሁንን በፔፔ ሰይዶ ፣ ፍፁም ፍትዓለውና አባይነህ ፌኖ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጥሩ ፉክክር ባስመለከተን የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫውን የወሰዱበት ነበር። ከማራኪ ፉክክር ውጭ ጥቂት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በታየበት አጋማሽ በወላይታ ድቻዎች በኩል አንድ በጣና ሞገዶቹ ደግሞ ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተደርገዋል። በአጋማሹ ከኳስ ውጭ እጅግ የተደራጀ አደራደር የነበራቸው የጣና ሞገዶቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰው በሀብታሙ ታደሰ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አጥቂው ያብስራ ተስፋዬ ያሻገረለትን ኳስ ተንሸራቶ ሲጨርፈው ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል።

ዘግይተው ወደ ጥሩ እንቅስቃሴ የገቡት የጦና ንቦች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ በነበሩባቸው ደቂቃ ላይ የተደራጀውን የባህርዳር ከተማ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በቢንያም ፍቅሬ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል፤ አጥቂው አብነት ደምሴ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ መቶ ለጥቂት የወጣበት ሙከራም ቡድኑ ከፈጠራቸው ዕድሎች የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች። በሰሣኛው ደቂቃም ባህርዳር ከተማዎች ከመዕዘን በተሻገረ ኳስ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አሳዳጊ ክለቡን የገጠመው ቸርነት ጉግሳ ከመዕዘን የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠርም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ በኋላ ወላይታ ድቻዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የአቻነት ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል።

የወላይታ ድቻ ሙሉ ብልጫ ባስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ የጦና ንቦች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው ሲጫወቱ ባህርዳር ከተማዎች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ አፈግፍገው የተጫወቱበት ነበር። አጋማሹም በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶችና እነሱን ተከትሎ በሚሰሙ ፊሽካዎች ታጅቦ ተካሂደዋል። የጦና ንቦቹ በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢይዙም በበርካታ ተጫዋቾች የተደራጀውን የባህር ዳር ከተማ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በቢንያም ፍቅሬ ድንቅ የመቀስ ምት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር፤ አጥቂው አበባየሁ ሀጂሶ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ በመቀስ ምት ቢመታውም ከረዥም ጊዜ በኋላ ቡድኑን በአምበልነት የመራው ያሬድ ባዬ ከመስመር መልሶበታል። በጥሩ አቋቋም የነበረው አናጋው የተመለሰውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራም ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮች አስወጥተው ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን በሚሰጡ የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት አጋማሹን የጀመሩት ባህርዳር ከተማዎች በአጋማሹ ያሳዩት ጥሩ የመከላከል ብቃት ሙሉ ሦስት ነጥብ አስገኝቶላቸው ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሀያ ሁለት ነጥብ ሰብስበው የመጀመርያውን ዙር አገባደዋል።