መረጃዎች| 61ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ዙር ጨዋታዎች ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይገባደዳል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

በተመሳሳይ ነጥብ የሚገኙ ሁለት ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ 09:00 ላይ ይጀምራል።

በአስራ ስምንት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ወደ ጥሩ ብቃት መጥተዋል። ቡድኑን ከተከታታይ ሽንፈቶች ወጥቶ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ድል ማስመዝገቡም የቡድኑ ወቅታዊ አቋም ማሳያ ነው። ሀዋሳዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻለ የማጥቃት አጨዋወት አላቸው፤ ዐሊ ሱሌይማን ዒላማ ባደረጉ ኳሶችና በፈጣን ሽግግሮች የተመሰረተ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ይህም በዋነኝነት በቡድኑ የሚጠቀስ ጠንካራ ጎን ነው። ሆኖም በነገው ጨዋታ የሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ጠጣር ቡድን እንደመግጠማቸው በፊት መስመር ላይ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይደለም።

በመጀመርያዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ባደረጓቸው አስራ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት ሀድያ ሆሳዕናዎች ሽንፈት አልባ ጉዟቸው ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሀድያዎች ምንም እንኳ ከአዳማ ከተማና መቻል በተመሳሳይ ጥቂት ሽንፈቶች ቢያስተናግዱም ያሸነፉት የጨዋታ መጠን ሦስት ብቻ ነው፤ ዘጠኝ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብም በብዙ ጨዋታዎች ነጥብ ተካፍሎ የወጣ የሊጉ ቡድን ነው። ሀድያዎች ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ቢያስተናግዱም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ግን ስልነት ይጎድልባቸዋል። ቡድኑ ፋሲል ከነማን ሁለት ለአንድ ካሸነፈበት ጨዋታ ወዲህ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን አራት ነው። ሀድያችዎ ባለፉት ሳምንታት ጠንካራ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ቡድኖች ገጥመው ለተጋጣሚ ፈተና የሆነ የመከላከል አደረጃጀት ነበራቸው፤ በነገው ዕለትም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ከሚገኘው የሀዋሳ ከተማ የፊት መስመር የሚያደርጉት ፍልምያ ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ተከላካዮቹ በረከት ወልደዮሐንስ እና ከድር ኩሊባሊ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሳተፉም።

በሊጉ በተገናኙባቸው ስምንት ግንኙነቶች (የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን አይጨምርም) ሀዋሳ 2 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሆሳዕና 1 አሸንፏል። በቀሪ 5 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 13፣ ሀዲያ ሆሳዕና 11 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በረዳት ዳኝነት ሲራጅ ኑርበገን ሚፍታህ ሁሴን አራተኛ ባህሩ ተካ ሆኖ ተመድቧል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

ብርቱካናማዎቹ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ሰራተኞቹ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ወጥተው ዙሩን ለማገባደድ የሚያደርጉት ጨዋታ የመጀመሪያው ዙር መቋጫ ይሆናል።

በአስራ ስድስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ብርቱካናማዎች ያለመሸነፍ ጉዟቸው ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ድሬዳዋ ከተማዎች በመቻል ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አልገጠማቸውም፤ አንድ ጨዋታ አሸንፈው በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። በተጠቀሱት ጨዋታዎችም በሁሉም ረገድ መሻሻል አሳይተዋል። በተለይም በመከላከሉ ረገድ ያሳዩት መሻሻል በጥሩነቱ ይነሳል። ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱም የዚ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ የተቀዛቀዘው የማጥቃት ክፍላቸው አሻሽለው ወደ ጨዋታው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

በአስር ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች የነገውን ጨዋታ ካሻነፉ ከወራጅ ቀጠናው ወጥተው የመጀመርያውን ዙር ያጠናቅቃሉ። ወልቂጤዎች ካሸነፉ ሰባት ሳምንታት ተቆጥረዋል፤ ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኃላ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች አምስት ሽንፈትና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበዋል። በነገው ዕለትም ከተከታታይ የአቻና ሽንፈት ውጤቶች ለመላቀቅና ከወራጅ ቀጠናው ወጥቶ ዙሩን ለማጠናቀቅ በተለየ መንፈስ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል። ሆኖም ባለፉት ሰባት ሳምንታት ሁለት ግቦች ብቻ ያመረተው የማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ለውጦች ማድረግ ግድ ይላቸዋል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ተመስገን ደረስ ፣ ዓብዱልፈታህና ያሲን ጀማል በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። የሲያም ሱልጣን መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ከዛ በተጨማሪ እያሱ ለገሰ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፍም። አሰጋኘኝ ጴጥሮስ ግን ከጉዳቱ አገግሞ ቡድኑን ያገለግላል። በወልቂጤ ከተማ በኩል አሜ መሐመድ እና ተመስገን በጅሮንድ በጉዳት አይኖሩም ፤ የመሳይ ጳውሎስ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 6 ጊዜ ተገናኝተው (የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን አይጨምርም) እኩል ሁለት ጊዜ ተሸናንፈው ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል። ወልቂጤ 9፣ ድሬዳዋ 8 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ዳንኤል ይታገሱ በመሐል ዳኝነት ደረጀ አመራ እና እሱባለው መብራቱ ረዳቶች እንዲሁም ኃይማኖት አዳነ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።