ሪፖርት | ነብሮቹ በአሥር የአቻ ውጤቶች ውድድሩን አጋምሰዋል

ሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሲገናኙ ኃይቆቹ በ14ኛው ሳምንት ሀምበርቾን 2ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አቤኔዘር ዮሐንስ እና ተባረክ ሄፋሞ በታፈሰ ሰለሞን እና አዲሱ አቱላ ተተክተው ሲገቡ ነብሮቹ በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት ባህር ዳር ከተማን 1ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ያሬድ በቀለ ፣ ዳግም ንጉሤ እና ካሌብ በየነ በታፔ አልዛየር ፣ አስጨናቂ ጸጋዬ እና ከድር ኩሊባሊ ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ገብተዋል።


ቀን 9 ሰዓት ላይ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ግሩም አጀማመር ያደረጉት ሀዲያዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሳሙኤል ዮሐንስ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው ቃለአብ ውብሸት በግንባር ገጭቶ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው መለሰ ሚሻሞ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ተገልብጦ በመምታት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ ሽግግር ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ሀዋሳዎች 25ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ሙከራቸውን ሲያደርጉ ኢዮብ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ ሲመልስበት ፈጣኑ አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ደግሞ 29ኛው እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ፈታኝ ያልሆኑ ሙከራዎችን አድርጎ ግብ ጠባቂው ያሬድ በድጋሚ ይዟቸዋል።

መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው ሲቀጥል ኃይቆቹ ከቆመ ኳስ ወደ አቻነት ተመልሰዋል። ኢዮብ ዓለማየሁ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ በግንባር ገጭቶ ወደ ወስጥ ሲቀንሰው ኳሱን ያገኘው ፀጋአብ ዮሐንስ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ግሩም አጀማመር ያደረጉት ነብሮቹ 50ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ሳሙኤል ዮሐንስ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ በተከላካዮች ከተመለሰ በኋላ ያገኘው ሰመረ ሀፍተይ ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በተከታታይ ደቂቃዎችም ነብሮቹ ሰመረን መዳረሻ ያደረጉ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተቀዛቅዘው የቀረቡት እና ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት የተቸገሩት ሀዋሳዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱሌይማን በግሩም ሁኔታ በተቆጣጥረው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪም ተጨማሪ የግብ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ነብሮቹ ግን 64ኛው ደቂቃ ላይ በመለሰ ሚሻሞ 67ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በካሌብ በየነ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አድርገው ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድን መፈተን አልቻሉም።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ይበልጥ እየተቀዛቀዘ እና የግብ ዕድሎችን ሳያሳየን በቀጠለው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተነቃቁት ኃይቆቹ 84ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማ የግብ ዕድል አግኝተው ዓሊ ሱሌይማን ከግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ የቀማውን ኳስ ያገኘው ተባረክ ሄፋሞ ለማመን በሚከብድ መልኩ ወደ ላይ በመምታት ክፍቱን ጎል ስቶታል። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃም የሀዋሳው በረከት ሳሙኤል ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሆኖም ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ መሃል ላይ ኳስ ይዘው የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ማጣታቸው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እንዳይኖራቸው ማድረጉን ሲገልጹ ተባረክ ሄፋሞ የሳተውን ኳስ “መሬትን በድንጋይ እንደመሳት” ነው ሲሉ የመጀመሪያው ዙር እንዳሰቡት እንዳልነበር እና ውል እያላቸው ለቡድኑ አገልግሎት እየሰጡ ያልሆኑ ተጫዋቾች በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጣቸው በመናገር በቂ የዕረፍት ጊዜ ባለመኖሩ አወዳዳሪው አካል እንዲያስብበት አበክረው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ቡድናቸው ግብ ካስቆጠረ በኋላ ውጤት ለማስጠበቅ በሚል እንደወረደ በመናገር ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያለመረጋጋት ችግር እንዳለባቸው እና ያም ጫና እንደፈጠረባቸው ሲጠቁሙ የውድድሩ ጅማሬ ላይ ጥሩ አጀማመር እንዳልነበራቸው እና ሪከርድ የሆነው 10 የአቻ ውጤትም አሳሳቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።