ሪፖርት | የሊጉ 120ኛ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ባለድል አድርጓል

ወልቂጤ ከተማዎች የውድድር ዘመኑን 9ኛ ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ በቻርለስ ሙሴጌ ብቸኛ ጎል 1ለ0 በማሸነፍ የአዳማ ቆይታቸውን በድል አገባደዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በ14ኛ ጨዋታ ሳምንት ከተጠቀሙት የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾች ተመሳሳይ የአራት ተጫዋቾችን ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎች እያሱ ለገሠ ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ሔኖክ አንጃው እና ኤፍሬም አሻሞን አስወጥተው በምትካቸው ቴዎድሮስ ሀሙ ፣ አቤል አሰበ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ዘርዓይ ገ/ስላሴ ሲተኩ በተመሳሳይ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ አዳነ በላይነህ ፣ መድን ተክሉ ፣ ጌቱ ሀይለማርያም እና ዳንኤል ደምሱን በሔኖክ ኢሳያስ ፣ ዳንኤል መቀጮ ፣ መሳይ ፓውሎስ እና ሙሉዓለም መስፍን በመተካት ቀርበዋል።

ከሰሞኑ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው የጨዋታ ታዛቢ ይድነቃቸው ዘውገ የህሊና ፀሎት በማድረግ የጀመረው የአንደኛው ዙር የማሳረጊያ መርሀግብር አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ መልክ የነበረው ቢመስልም ድሬዳዋ ከተማዎች ግን በሂደት በተለይ በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ ያስተዋልንበት ነበር።

12ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች በመሐመድ አብዱልጋኒዮ አማካኝነት ከቅጣት ምት አደገኛ ሙከራን ቢያደርጉም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰችበት ኳስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከተመለከትናቸው ሙከራዎች አጅግ አደገኛዋ አጋጣሚ ነበረች።

ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደርጉ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች 29ኛው ደቂቃ በዚሁ የጨዋታ መንገድ አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢያገኛም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት ድሬዎች በ30ኛው ደቂቃ መሪ ሆነዋል ፤ ከሱራፌል ጌታቸው የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ቻርለስ ሙሴጌ በቀላሉ በማስቆጠር ድሬን ቀዳሚ አድርጓል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ወልቂጤዎች ጋዲሳ በረጅሙ ያሻገረውን የቅጣት ምት ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ሳኒ በግንባር አስቆጠረ ሲባል ባመከናት ኳስ አጋማሽ በድሬዳዋ መሪነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ወልቂጤዎች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ የጀመሩት ሲሆን እነዚህም ለውጦች ቡድኑ ላይ በእንቅስቃሴ ደረጃ የሚታዩ ለውጦችን ማምጣት የቻሉ ቢሆንም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የማጥቃት ጨዋታቸው ጥራት ግን ፍፁም ደካማ ነበር።

ድሬዳዋ ከተማዎች ይበልጥ በጥንቃቄ በተጫወቱበት በዚሁ አጋማሽ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የወልቂጤው አማካይ መድን ተክሉ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታት እንዲሁም አብዩ ካሳዬ በድንቅ ሁኔታ ካዳነበት ኳስ ውጭ ጠቃሽ ሙከራዎች አልነበሩትም። በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ጨዋታው የተቋጨው ጨዋታ ውጤት ለድሬዳዋ ከተማ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ድል ሆኖ ሲመዘገብ በአንፃሩ ለወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ የዓመቱ ዘጠነኛ ሽንፈትን ሆኗል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ለማሸነፍ በጥቃቅን ስህተቶች መሸነፋቸውን ገልፀው በአዳማ የ15 ሳምንት ቆይታቸው በውጤት ደረጃ ደስተኛ አለመሆናቸውን ጠቅሰው በድሬዳዋ በቀጣይ በሚደረገው ውድድር ግን ተሻሽለው እንደሚቀርቡ አስረድተዋል።የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ በበኩላቸው በውጤቱ በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ ሊጉ ወደ ድሬዳዋ ስለሚሄድ ወደ ለዚያ ትልቅ የሞራል ስንቅ የሚሆን ውጤት መሆን ገልፀዋል።