ኢትዮጵያ መድን ሁለተኛ ተጫዋቹን አስፈርሟል

በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ጅማ አባጅፋር የስድስት ወራት ቆይታ የነበረው አማካይ አዲሱ የኢትዮጵያ መድን ፈራሚ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር የውድድር መርሀግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀመር ኢትዮጵያ መድን በቀዳሚ መርሀግብሩ ባህርዳር ከተማን ያስተናግዳል። በሊጉ የመጀመሪያው ዙር ደካማ አቋምን ሲያስመለክተን የነበረው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌው ኢትዮጵያ መድን በሁለተኛው ዙር የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት ከቀናት በፊት ተከላካዩ ሚሊዮን ሠለሞንን የግላቸው ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ ወጣቱን የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አናንያ ጌታቸውን በይፋ ቡድኑ ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።

በቅርቡ ለድሬዳዋ ስታዲየም ምርቃት ኢትዮጵያ ዩጋንዳን በገጠመችበት ጨዋታ ጥሪ ደርሶት ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን ያገለገለው በአጥቂ አማካይ እና በተከላካይ አማካይ ስፍራ በአውስኮድ ፣ ዳሞት ከተማ እና ላለፉት ስድስት ወራት ደግሞ በጅማ አባጅፋር በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ጥሩ የውድድር ጊዜን ያሳለፈው ተጫዋቹ ከቀናት በፊት ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ያደረጉለትን አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌን ጥሪን ተቀብሎ ኢትዮጵያ መድንን በይፋ ተቀላቅሏል።