የመጀመርያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ  ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

👉ብዙ ደቂቃ የተጫወቱ ተጫዋቾች

👉 የመጀመርያው ዙር ፈጣን ግቦች

👉በርካታ ግቦች ያስተናገዱ ግብ ጠባቂዎች

ቀደም ብለን ክለቦች የተመለከቱ መረጃዋች ማቅረባችን ይታወሳል አሁን ደግሞ ተጫዋቾች የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎች አቅርበንላችኋል


ተጫዋቾችን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች

ብዙ ደቂቃ የተጫወቱ ተጫዋቾች

በተካሄዱት አስራ አምስት ጨዋታዎች በእያንዳንዱ ደቂቃዎች ሜዳ ውስጥ የነበሩና ለ1350 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆዩት ተጫዋቾች አስራ ሁለት ናቸው። የወላይታ ድቻዎቹ ቢንያም ገነቱ እና ናትናኤል ናሴሮ ፣ የሻሸመኔ ከተማዎቹ አሸብር ውሮ እና የአብሥራ ሙሉጌታ ፣ የመቻሉ ግብ ጠባቂ አልዌንዚ ናፊያን ፣ ጋናዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ፣ የፋሲል ከነማው መናፍ ዐወል ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ፈቱዲን ጀማል ፣ የድሬዳዋ ከተማ ሁለት የውጭ ተጫዋቾች አብዱልለጢፍ መሐመድና ኢስማኤል አብዱልጋኒዩ እንዲሁም የአዳማ ከተማዎቹ ሰይድ ሀብታሙና ፍቅሩ ዓለማየሁ ሳይቀየሩ በሁሉም ጨዋታዎች ተሳትፎ የነበራቸው ተጫዋቾች ናቸው።

የመጀመርያው ዙር ፈጣን ጎሎች

በግማሽ የውድድር ዓመት ቆይታ በርከት ያሉ ፈጣን ጎሎች ተመዝግበዋል። ከነዚህ ውስጥ ግን የድሬዳዋ ከተማው ኤፍሬም አሻሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ያስቆጠራት ግብ የሊጉ ፈጣን ግብ ሆና ተመዝግባለች።  የባህርዳር ከተማው አለልኝ አዘነ በሦስተኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ  ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ፣ የሀድያ ሆሳዕናው ሰመረ ሀፍታይ እና የሀዋሳ ከተማው ተባረክ ሄፋሞ በተመሳሳይ ወላይታ ድቻ ላይ በሦስተኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠሯቸው ግቦች ደግሞ ሌሎች ፈጣን ጎሎች ናቸው።

በርካታ ግቦች ያስተናገዱ ግብ ጠባቂዎች

በመጀመርያው ዙር በርካታ ግቦች ያስተናገደው ግብ ጠባቂ የኢትዮጵያ መድኑ አቡበከር ኑራ ነው። በአስራ አምስት ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት የጀመረውና 1349 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆየው ይህ ግብ ጠባቂ ሀያ ሁለት ግቦች አስተናግዷል። ይህ ማለት በየ ስልሣ አንድ ደቂቃው ግብ ተቆጥሮበታል። ግብ ጠባቂው በተመስገን ዮሐንስ ተቀይሮ በመውጣቱ ካመለጠው አንድ ደቂቃ ውጭ በእያንዳንዱ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ቆይቷል። በዙሩም በሦስት ጨዋታዎች ላይ ግቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሏል።  ከአቡበከር ኑራ በመቀጠል በርካታ ግቦች ያስተናገደው ተጫዋች የሻሸመኔ ከተማው ግብ ጠባቂ ኬን ሳይዲ ነው። በአስራ ሦስት ጨዋታዎች ተሳትፎ የነበረው ይህ ግብ ጠባቂ አስራ ሰባት ግቦች አስተናግዷል። በሦስተኛ ደረጃነት የተቀመጡት ደግሞ የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰይድ ሀብታሙ እና የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ በአሥራ ስድስት ጎሎች ነው።


በርካታ ካርዶች የተመለከተ ተጫዋች

በመጀመርያው ዙር በተካሄዱት ጨዋታዎች በርካታ ካርዶች የተመለከቱት የሀድያ ሆሳዕናው ተከላካይ ዳግም ንጉሴና የንግድ ባንኩ ሱሌይማን ሀሚድ ናቸው። ተጫዋቾቹ እያንዳንዳቸው አስር ካርዶች ተመዞባቸዋል። ዳግም ንጉሴ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ከወጠበት ጨዋታ ጨምሮ አስር የቢጫ ካርዶች ተመልክቷል፤ ሱሌይማን በበኩሉ በሁለት ጨዋታዎች በሁለት ቢጫ ከሜደ ወጥቷል። ዘጠኝ ካርዶች የተመዘዘባቸው ፍሬዘር ካሳ፣ የሀዋሳ ከተማዎቹ መድሀኔ ብርሃኔና እዮብ አለማዮህ ደግሞ ከሁለቱ ተጫዋቾች በመቀጠል በርካታ ካርዶች የተመለከቱ ተጫዋቾች ሆነዋል።