ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ነገ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታን ይመራሉ

አራት ኢትዮጵያዊያን ኢንተርናሽናል ዳኞች ነገ አልጄሪያ ላይ የሚደረገውን የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታን በዳኝነት ይመሩታል።

የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ መርሀግብሮች በነገው ዕለት በሚደረጉ ጨዋታዎች እስከ ዕሁድ ድረስ ይዘልቃሉ። ነገ ዕርብ ምሽት 1፡00 በአልጄሪያዋ ቤን አክኖን በሚገኘው ስታድ ዱ ፋይፍ ጁሊየት ስታዲየም በምድብ አራት ስር የሚገኙትን ባለ ሜዳው ሲ አር ቤሎይዝዳድን ከጋናው ሜዴማ ጋር የሚያገናኘውን ጨዋታ አራት ኢትዮጵያዊያን ኢንተርናሽናል ዳኞች በዳኝነት እንዲመሩት መመረጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በመሐል ዳኝነት በአምላክ ተሰማ ሲመራ ረዳቶቹ በመሆን ትግል ግዛው እና ተመስገን ሳሙኤል እንዲሁም ደግሞ በላይ ታደሠ አራተኛ ዳኛ ሆኖ በጣምራ ይህንን ጨዋታ እንዲመሩ ካፍ መድቧቸዋል። በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በጋናው ሜዴአማ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት መቋጨቱ የሚታወስ ሲሆን ከምድቡ ቀደም ብለውም መውደቃቸው ይታወቃል።