ሪፖርት | ባህር ዳር እና መድን ነጥብ ተጋርተዋል

በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን 0-0 ተለያይተዋል።

የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ 10፡00 ላይ በባህር ዳር ከተማ እና በኢትዮጵያ መድን መካከል ሲደረግ የጣና ሞገዶቹ በ15ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን 1ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ፍራኦል መንግሥቱ እና ከሀዋሳ በዚህ ሳምንት ቡድኑን የተቀላቀለው ሙጅብ ቃሲም በፍጹም ፍትሕዓለው እና በፍሬው ሰለሞን ተተክተው ሲጀምሩ መድኖች በተመሳሳይ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር 2-2 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሙሴ ከበላ እና ብሩክ ሙሉጌታ በአብዱልከሪም መሐመድ እና ንጋቱ ገብረሥላሴ ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባህር ዳሮች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን መውሰድ ቢችሉም የመድንን የኋላ መስመር ለማስከፈት ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም 9ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ ከረጅም ርቀት ለማሻማት በሚመስል መልኩ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ አስወጥቶበታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል አልፎ አልፎ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት መድኖች 14ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ መሬት ለመሬት የመታው ኃይል የለሽ ኳስ ግብ ጠባቂውን ፔፔ ሰይዶን መፈተን አልቻለም። በተጨማሪም የመስመር አጥቂው መሐመድ አበራ ሁለት ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ ነበር።

መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ 31ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ሀብታሙ ታደሰ በደረቱ ባበረደው ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ይዞበታል። በሦስት ደቂቃዎችም የአጋማሹ የተሻለ የግብ ዕድል በኢትዮጵያ መድን አማካኝነት ሲፈጠር አቡበከር ወንድሙ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሩክ ሙሉጌታ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ የጣና ሞገዶቹ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመግባት ተጭነው ለመጫወት ሲጥሩ 51ኛው ደቂቃ ላይም የተሻለውን ሙከራ አድርገዋል። አለልኝ አዘነ በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ በቀጥታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ አስወጥቶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ባሻገረው ኳስ ቸርነት ጉግሣ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

በመጨረሻዎቹ 25 ደቂቃዎች የጨዋታው ግለት ተሻሽሎ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። በተለይም 70ኛው ደቂቃ ላይ የባህር ዳሩ ቸርነት ጉግሳ በሳጥኑ የግራ ክፍል ከማቀበል አማራጭ ጋር ይዞት በገባው ኳስ ያደረገው ሙከራ ግብ ጠባቂውን መፈተን ሳይችል ሲቀር ከአንድ ደቂቃ በኋላ ተቀይሮ የገባው ፍሬው ሰለሞን ከግብ ጠባቂ ጋር ከሳጥን አጠገብ ተገናኝቶ ወርቃማ የግብ ዕድል ቢያገኝም ኳሱን ራሱ ግብ ጠባቂው መልሶበት ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

መሃል ሜዳው ላይ ቀስ በቀስ በተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው መጫወት የቻሉት መድኖች 77ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው መሐመድ አበራ ከመሃል በተሰነጠቀለት ኳስ ግብ ጠባቂውን ፔፔ ሰይዶን አታልሎ ማለፍ ቢችልም ደካማ በሆነ አጨራረስ ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል። በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎበት ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ውጤት ይዘው ለመውጣት እንደገቡ እና ውጤቱንም ማግኘት ይችሉ እንደነበር ሆኖም በራሳችው ችግር ማጣታቸውን በመናገር በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ማቀዳቸውን እና ነጥቡም በቂ እንደሆነም ሲገልጹ የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ከዓየር ንብረቱ ጋር በተገናኘ ፈታኝ ጨዋታ እንደነበር እና 4-4-2 አሰላለፍ ይዘው ገብተው ወደ 4-3-3 መቀየራቸውን በመግለጽ አዲስ የፈረሙ ልጆች ላይ ከጨዋታ ዝግጁነት አንጻር የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማየታቸውን ጠቁመዋል።