መድን ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች አማካይ እና የግብ ዘብ ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር ከነበረበት ዝቅታ ለመሻሻል በአጋማሽ የዝውውር መስኮት በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። ባለፉት ቀናትም ሚሊዮን ሠለሞን እና አናንያ ጌታቸው ቡድኑን የተቀላቀሉ ሲሆን የዝግጅት ክፍላችን አሁን በደረሳት መረጃ መሰረት ደግሞ ቡድኑ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አግኝቷል።

መድንን የተቀላቀለው ሦስተኛው ተጫዋች አማካዩ ሀይደር ሸረፋ ነው። የቀድሞ የደደቢት፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንድርታ ተጫዋች አራት ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ከቆየ በኋላ ክረምት ላይ ወደ አዳማ ከተማ አምርቶ የነበረ ቢሆንም ከክለቡ ጋር ከግማሽ ዓመት በላይ ሳይቆይ ከቀድሞ አሠልጣኙ ጋር ዳግም ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርቷል።

ሌላኛው የመድን አዲስ ተጫዋች ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ነው። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡና እና መቻል ተጫዋች እንደ ሀይደር ክረምት ላይ አዳማን ተቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም ከክለቡ ጋር መቀጠል ሳይችል መልቀቂያውን በመውሰድ ወደ መድን አምርቷል።

ሁለቱም ከአዳማ ወደ መድን ያመሩ የቡድን አጋሮች ከአዳማ ጋር ያላቸውን ውል አፍርሰው የአንድ ዓመት ተኩል ውል በፌዴሬሽን ተገኝተው እንደፈረሙም ተረጋግጧል።