ጀማል ጣሰው ወደ ቀድሞው ክለቡ አምርቷል

    አንጋፋው የግብ ዘብ ወደ አዳማ ከተማ ማምራቱ ሲታወቅ ጋናዊው ተከላካይ ከክለቡ ጋር አይገኝም።

    የፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያውን ዙር የአስራ አምስት ሳምንታት ጨዋታን በሜዳው ያከናወነው አዳማ ከተማ ያሉበት የውስጥ ችግሮች በተወሰነ መልኩ እየተቀረፉለት የሚገኝ ሲሆን የፊታችን ዕሁድ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በሁለተኛው ዙር የሊጉ የመክፈቻ መርሀግብር እንደሚገጥም ይጠበቃል።

    ቡድኑ በትላንትናው ዕለት አማካዩ ሀይደር ሸረፋ እና ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆን ለኢትዮጵያ መድን አሳልፎ የሰጠ ሲሆን በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ያለበትን ክፍተት ለመድፈን ከክለቡ ጋር የዝግጅት ጊዜን ለሳምንታት ሲያሳልፍ የነበረውን አንጋፋውን ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰውን ክለቡ በድጋሚ ወደ ስብስቡ ስለ ማካተቱ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።

    ከኢትዮ ኤሌክትሪክ መነሻውን ካደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ደደቢት ፣ መቻል ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ጅማ አባ ቡና ፣ አዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው የግብ ዘቡ ወደ ቀደመ ክለቡ አዳማ ማምራቱ ዕውን ሆኗል።

    ከአዳማ ከተማ ጋር በተያያዘ ጋናዊው የመሐል ተከላካይ ሐቢብ መሐመድ ከክለቡ ጋር በተፈጠረ የክፍያ አፈፃፀም ክፍተት ወደ ሀገሩ መመለሱ የተሰማ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ተጫዋቹን አግኝታ ጉዳዩን ለማጥራት ብትሞክርም ተከላካዩ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት እንደማይፈልግ ከጋና አስረድቶናል።