ሪፖርት | የተመስገን ብርሀኑ ጎል ሀድያ ሆሳዕናን አሸናፊ አድርጋለች

አምስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስተው መቻልን 3-2 በመርታት ጣፋጭ ድልን አግኝተዋል።

በሊጉ የ15ኛ የጨዋታ ሳምንት ወቅት መቻሎች ሻሸመኔ ላይ ድልን ባስመዘገቡበት ወቅት ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ ፍፁም ዓለሙን በዮሐንስ መንግስቱ ሲተኩ ከሀዋሳ ጋር ነጥብ ተጋርተው በነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል በተደረገ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ቃልአብ ውብሸት ፣ ካሌብ በየነ እና ከክለቡ የተለያየው ስንታየሁ ዋለጪን በበረከት ወልደዮሐንስ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ኩሊባሊ ከድር ተተክተው ቀርበዋል።

ጨዋታውን የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ቢሆኑም የነጠቁትን ኳስ በአግባቡ ተጠቅመው ገና በጊዜ ጎል ያስቆጠሩት መቻሎች ሆነዋል። 2ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ ከቀኝ ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ በአግባቡ የተቆጣጠረው አቤል ነጋሽ ከሳጥኑ ጠርዝ በመምታት ያሬድ በቀለ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ቢቸገሩም ረጃጅም ኳስን ተጠቅመው ጎል ካስተናገዱ ለመጫወት የጣሩት ሀድያዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ ተቃርቀው ነበር። ሳሙኤል ዮሐንስ ከግራ በኩል ወደ መስመር ካደላ ቦታ የተገኘን የቅጣት ምት አሻምቶ ዳዋ ሆቴሳ በግንባር ገጭቶ የግቡን የላይኛውን ብረት ኳሷ ታካ ወጥታለች።

ጥንቃቄ ላይ አመዝነው በቅብብል በቀላሉ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት መቻሎች የአማካይ ተጫዋቾቻቸውን ጥምረት በመጠቀም ወደ ሳጥን በሚላኩ ኳሶች ተጨማሪ ጎልን ለማስቆጠር በተሻለ ብልጫን በመያዝ መንቀሳቀስ ችለዋል። 16ኛው ደቂቃ ከነዓን ከራሱ የሜዳ ክፍል እየነዳ ወደ ሀድያ ግብ ክልል ያደረሳትን ኳስ በቀኝ ቦታ ነፃ ለነበረው ቺቺኦኪ አኩኔቶ አቀብሎት አጥቂው ወደ ጎል መትቶ ግብ ጠባቂው ያሬድ በጥሩ ብቃት ኳሷን አድኖበታል። 25ኛው ደቂቃ ላይም ሽመልስ በቀለ ያደረጋት እና ያሬድ በቀለ ተቸግሮ የያዘት ኳስ ትጠቀሳለች።

ቀስ በቀስ በሽግግር የጨዋታ መንገድ በይበልጥ ወደ ጨዋታ የገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች አከታትለው ጫና የሚያሳድሩ ጥቃቶችን ፈፅመዋል። 32ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ የግቡን ቋሚ ኳሷ ገጭታ ከተመለሰች ከአንድ ደቂቃ ቆይታ መልስ ሠመረ ከቀኝ ወደ ኋላ ያቀበለውን ኳስ ሔኖክ አርፊጮ በቀጥታ ወደ ጎል ሲያሻግር መለሠ ሚሻሞ በግንባር ገጭቶ ሀድያ ሆሳዕናን ወደ አቻነት ያሸጋገረች ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ሔኖክ አርፊጮ ወደ ጎል ያሻማት ኳስ አቅጣጫ ቀይራ ወደ ጎል ስታመራ ግብ ጠባቂው አሊዮኒዚ ናፊያን እንድምንም ኳሷን ከተቆጣጠራት በኋላ ጨዋታው በ1ለ1 የአቻ ውጤት ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ከፉክክር አኳያ ወረድ ያለ መልክን ቢይዝም ከደቂቃ ደቂቃ ግን ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁሉ መቻሎች ሻል ያለ የጨዋታ ጊዜን ሜዳ ላይ አሳልፈዋል። ኳስን ከአማካይ ክፍል ወደ መስመር በመለጠጥ በጥልቅ የጨዋታ መንገድ ጎል ለማስቆጠር የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት መቻሎች 60ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ወደ ጎል እየሄደች ያለችን ኳስ ግሩም ሀጎስ ለመያዝ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ሠመረ ሀፍታይ በሳጥን ውስጥ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችን የፍፁም ቅጣት ምት ከነዓን ወደ ግብነት በቀላሉ ለውጧታል።

ከጎሏ በኋላ መቻሎች ምንይሉ እና በረከትን ሀድያ ሆሳዕና በበኩላቸው በየነ እና ተመስገንን ወደ ሜዳ ያስገቡ ሲሆን ሀድያዎች ከመከላከል መዋቅራቸው በይበልጥ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ጨዋታ ለመግባት ያደረጉት ጥረት ከቆመ ኳስ ተሳክቶላቸዋል። 70ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የሜዳ ክፍል ወደ መስመር ጥቂቱን ከተጠጋ ቦታ የተገኘን የቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ከማሻማት ይልቅ መሬት ለመሬት በግራ የሰጠውን ሔኖክ አርፊጮ በቀጥታ ወደ ግብ የላከትን ኳስ ግሩም ሀጎስ ለማውጣት ሲጥር በራሱ መረብ ላይ ኳሷን አስቀምጧታል።

ወደ መሪነት ለመሸጋገር ይበልጥ ሜዳ ላይ ከሚታዩ ጥድፊያዎች እና መቻኮሎች ውጪ ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ለመመልከት የመጨረሻ ደቂቃን ለመጠበቅ በተገደድንበት ጨዋታ 86ኛው ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕና ሦስት ነጥብን ማሳካታቸውን ያረጋገጡበቶን ግብ አግኝተዋል። ዳዋ ሆቴሳ እግሩ ስር የደረሰችውን ኳስ በመቻል ተከላካዮች መሐል አሾልኮ ሲሰጠው ተቀይሮ የገባው ተመስገን ብርሀኑ በጥሩ አጨራረስ ይዞ የገባትን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ በመጨረሻም ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በጨዋታው ጥሩ አልነበርም ካሉ በኋላ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖረንም ብቻውን ውጤት አያስገኝም የተቀጠሩብንም ጎሎች በራሳችን ስህተት የተገኙ ናቸው በማለት በቀጣይም ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል። የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ጠቁመው በማጥቃቱ እንደተሳካላቸው እና ሁለቴ ተመርተው ሁለቴ ጎል ማስቆጠራቸው ማሳያ እንደሆነ እንዲሁም የተሻለ ጨዋታም እንደነበር ጠቅሰዋል።