የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ16ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

አቤል ማሞ – ሻሸመኔ ከተማ

ሻሸመኔዎች ከመመራት ተነስተው ወላይታ ድቻን 2ለ1 ሲያሸንፉ ሦስተኛ ጨዋታውን ያደረገው የግብ ጠባቂያቸው ብቃት እጅግ አስደናቂ ነበር። ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ በሙሉ ትኩረት ጨዋታውን ሲያደርግ የነበረው አቤል በርካታ ያለቀላቸውን ኳሶች በማዳኑም ባሻገር የቀድሞ አቋሙን ፈልጎ ለማግኘት እየታተረ ከመሆኑ አንፃር በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ያለ ተቀናቃኝ ለመካተት ችሏል።

ተከላካዮች

ዳግማዊ ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ብርትካናማዎቹ በአዲስ መልክ በተሠራው የመጫወቻ ሜዳቸው በደጋፊያቸው ፊት ሁለተኛውን ዙር ሀምበርቾን በመርታት በድል ሲጀምሩ ለተቆጠረችው ብቸኛ ጎል የተከላካዩ ሚና ግንባር ቀደሙን ድርሻ ይወስዳል። በመጀመርያ አሰላለፍ ከገባበት ያለፉት ሰባት ሳምንታት ወዲህ በየጨዋታው ራሱን በማሻሻል በሚያሳየው ጥሩ ግልጋሎት በቦታው ቀዳሚ ተመራጭ የሆነው ዳግማዊ ለሁለተኛ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ አስራ አንድ ስብስብ ውስጥ ሊካተት ችሏል።

ኢዮብ ማቲያስ – ፋሲል ከነማ

በሰባተኛው ሳምንት ፋሲል ከነማ ከወላይታ ድቻ ጋር ካደረገው ጨዋታ በኋላ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የገባው ኢዮብ ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን ከመመራት ተነስቶ በረታበት ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ የነበረው ሚና መልካም የሚባል ነበር። ምንም እንኳን ከዕረፍት መልስ ሀዋሳዎች በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ ክፍል በዝተው ቢከላከሉም አልፎ አልፎ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በማቋረጥ እና ለአማካይ ክፍሉ ትክክለኛ ኳሶችን በማቀበል የማጥቃት  እንቅስቃሴውን በማሳለጥ ያሳየው ሚና የጎላ በመሆኑ በምርጫ ውስጥ ሊካተት ችሏል።

ወንድሜነህ ደረጄ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታ ብልጫ ጋር ሲዳማ ቡና ላይ በተቀዳጀው ድል የኋላ መስመር ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጄ ጥሩ የጨዋታ ጊዜን አሳልፏል። ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ቡናማዎቹን በጥሩ አቋም በማገልገል የኋላ ደጀን መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ተከላካዩ የሲዳማን የማጥቃት ኃይል በአግባቡ ከመከተባቸው መንገዶች አኳያ በምርጥ ስብስባችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።

ሔኖክ አርፊጮ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ የሊጉን መሪ መቻልን ድል ባደረገበት ጨዋታ የግራ መስመር ተከላካዩ ለውጤቱ ማማር ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። ቡድኑ እየተመራ አቻ የሆነበትን እና በድጋሚ ተመርቶ ወደ አቻነት ለመጣባቸው ሁለት ወሳኝ ጎሎች መገኘት በማቀበሉ የነበረው አበርክቶ ላቅ ያለ ድርሻ ከመሆኑም ባለፈ ለወጣት ተጫዋቾች በአንበልነት ድርሻው ለቡድኑ እየሰጠ ያለው አበርክቶ እየጨመረ መጥቷል።

አማካዮች

መለሠ ሚሻሞ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና ድል ባደረገበት ሳምንት የአማካይ ተጫዋቹ አብረውት ከሚሰለፉ የቡድን ጓደኞቹ ጋር ኳስን በአግባቡ በመቆጣጠር እና ቡድኑም ሲመራ በነበረበት ወቅት ወደ አቻነት ያሸጋገረች ድንቅ ግብ ማስቆጠር ችሎም ነበር። መለሰ በተደጋጋሚ በየጨዋታው ጎል በማስቆጠር የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ከመሆኑ ባለፈ ለሁለተኛ ጊዜ በሶከር ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ መካተት አስችሎታል።

አብዱልከሪም ወርቁ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና በቡናው ደርቢ ወሳኝ ነጥብን ሲጨብጥ ትንሹ ቅመም አብዱልከሪም ደምቆ አምሽቷል። ምንም እንኳን ሲዳማዎች በራሳቸው ላይ የመጀመሪያ ጎልን ቢያስቆጥሩም ኳሷ ወደ ጎልነት እንድትለወጥ አክርሮ ወደ ጎል በመምታት እንዲሁም ሁለተኛዋን የአዕምሮ ሥራ የሆነች ግሩም ግብ ማስቆጠር በመቻሉ ያለ ተቀናቃኝ የሳምንቱ ምርጣችን ውስጥ ተካቷል።

ቢኒያም በላይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የዓምናው የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ቢንያም በላይ ከጉዳት ጋር ተያይዞ የዓምናውን አቋም ለመድገም ቢቸገርም አሁን ወደ ትክክለኛው ትራክ የገባ ይመስላል። ፈረሰኞቹ ወልቂጤ ከተማን 2ለ0 ሲያሸንፉ የአማካዩ ብቃት የሚደነቅ ነበር። በርካታ ያለቀላቸውን ኳሶች በግሩም ዕይታ ሰንጥቆ እያቀበለ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠሩ ባሻገር ለመጀመሪያው የአማኑኤል ኤርቦ ጎል ከማዕዘን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

አጥቂዎች

መስፍን ታፈሠ – ኢትዮጵያ ቡና

ዕረፍት አልባ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ መስፍን ታፈሰ ቡናማዎቹ ወደ ግራ የሜዳው ክፍል የጥቃት መነሻቸው አድርገው በተጫወቱበት የጨዋታ ሳምንት የመስፍን ታፈሠ በዚህ ቦታ ተሰልፎ መጫወት ቡድኑ ለወሰደው ብልጫ ተጫዋቹ ትልቅ አበርክቶ የነበረው ሲሆን ሦስተኛዋ ጎልም ስትቆጠር ለብሩክ ከማቀበሉ አንፃር ሊካተት ችሏል።

ዳዋ ሆቴሳ – ሀዲያ ሆሳዕና

በጨዋታ ሳምንቱ ሀድያ ሆሳዕና ድልን ባስመዘገበበት ወቅት አጥቂው ዳዋ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። በማጥቃቱ ከተሰጠው ቀዳሚ ተሳትፎ ወደ መከላከሉ በማዘንበል ቡድኑን ሲረዳ የነበረው ተጫዋቹ የማሸነፊያዋን ግብ ተመስገን ብርሃኑ ባስቆጠረበት ወቅት በጥሩ ዕይታ ያቀበለበት መንገድ እንዲሁም ለሁለተኛው ግብ ቁልፍ መነሻ የነበር በመሆኑ በምርጥነት ተካቷል።

ስንታየሁ መንግሥቱ – ሻሸመኔ ከተማ

ከአሰልጣኝ ዘማርያም ቡድኑን መረከብ በኋላ በየጨዋታዎቹ መሻሻል በማሳየት ራሱን በሊጉ ለማቆየት እየጣረ የሚገኘው ሻሸመኔ ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻን ድል ባደረገበት ወቅት የአዲስ ፈራሚያቸው የስንታየሁ አስተዋጽኦ የጎላ ነበር። ተጫዋቹ ክለቡን በተቀላቀለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመጀመሪያ ጨዋታው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በብርቱ ከመታገል ባሻገር አንድ ጎል ማስቆጠሩ ቡድኑን ወደ ጨዋታው በመመለሱ ጭምር ምርጫ ውስጥ ሊካተት ችሏል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ከመመራት ተነስተው ወሳኙን ድል ሀዋሳዎችን በመርታት ሲያሳኩ የአሰልጣኝ ውበቱ ብስለት የተሞላበት አጨዋወት ዐይነተኛውን ሚና ይወስዳል። ከዕረፍት በኋላ ሀዋሳዎች ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ውስጥ መሆናቸውን ተከትሎ የተጋጣሚን አጥር ለማስከፈት ክፍት ቦታዎችን ፍለጋ ትዕግስት የተሞላበት ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችሉ እንዲሁም የአቤል እንዳለ እና ቃልኪዳን ዘላለም ቅያሪ ለውጤቱ ማማር ስኬታማ በመሆኑ አሰልጣኝ ውበቱን ከአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ጋር ተፎካክረው ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።


ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን
ሱሌይማን ሀሚድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ጋቶች ፓኖም – ፋሲል ከነማ
አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና
ጌትነት ተስፋዬ – ሻሸመኔ ከተማ
አሸናፊ ጥሩነህ – ሻሸመኔ ከተማ
ቃልኪዳን ዘላለም – ፋሲል ከነማ