ድሬዳዋ ከተማ ተጨማሪ ተጫዋች አስፈርሟል

በትናንትናው ዕለት አሜ መሐመድን ያስፈረመው ድሬዳዋ ከተማ ዛሬ ደግሞ ተጨማሪ አንድ ተጫዋች ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ከ16 እስከ 22ኛ ሳምንት ድረስ በአዲሱ ሜዳቸው የሚጫወቱት ድሬዳዋ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር በተለይ በፊት መስመር ያለባቸውን ክፍተት አሻሽሎ ለመቅረብ በዝውውር መስኮቱ እያማተሩ የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም አሜ መሐመድን ከወልቂጤ ከተማ አስፈርመው ከተጫዋቹ ጋር ልምምድ መጀመራቸውን ዘግበን ነበር። ክለቡ አሁን ደግሞ ከታችኛው የሊግ እርከን ተጨማሪ የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋች ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች ናትናኤል ዳንኤል ነው። የፊት አጥቂም ሆነ የመስመር አጥቂ በመሆን የሚጫወተው የቀድሞ የሾኔ ከተማ እና ቦዲቲ ከተማ ተጫዋች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በቡራዩ ከተማ ቆይታ አድርጓል። አሁን ደግሞ በድሬዳዋ የተሰጠውን የሙከራ ጊዜ አጠናቆ ለክለቡ መፈረሙ ተረጋግጧል።