ዐፄዎቹ ሁለት ተጫዋቾች አስፈርመዋል

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ፋሲል ከነማ የማጥቃት እና የመከላከል ባህሪ ያላቸው ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተን በመቅጠር ሊጉን የጀመሩት ዐፄዎቹ በ16 ጨዋታዎች 26 ነጥቦችን በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጡ ይታወቃል። ክለቡ በሁለተኛው ዙር የበለጠ ተጠናክሮ ለመቅረብ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ግልጋሎት የሚሰጡትን ሁለት ተጫዋቾች ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ፋሲልን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ ነው። ጋናዊው የቀድሞ አሻንቲ ጎልድ፣ አሳንቲኮቶኮ እና ድሪምስ ተከላካይ ዓምና ኢትዮጵያ መድንን በመቀላቀል የሀገራችንን ሊግ የተዋወቀ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ደግሞ ወደ አዳማ ከተማ አምርቶ ነበር። ተጫዋቹ ከክፍያ ጋር በተያያዘ ከአዳማ ከተማ ጋር ሳይስማማ ቀርቶ ውሉን በማፍረስ ለፋሲል ፊርማውን አኑሯል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ አጥቂው አፍቅሮት ሰለሞን ነው። የእግርኳስ ህይወቱን መነሻ በደደቢት ተስፋ ቡድን ያደረገው አፍቅሮት በዋናው ቡድን የተወሰነ ጊዜ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መድን እና ገላን ከተማ አምርቶ የተጫወተ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ በሀምበሪቾ ቤት ጥሩ ጊዜ አሳልፎ አሁን መዳረሻው ፋሲል ሆኗል።