ከፍተኛ ሊግ | አስራት አባተ ቢሾፍቱ ከተማን ሲረከብ ቡድኑም ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስር የሚገኘው ቢሾፍቱ ከተማ አሰልጣኝ አስራት አባተን በኃላፊነት ሲሾም አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችንም አስፈርሟል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ተሳታፊ የሆነው ቢሾፍቱ ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ 12ኛ ላይ በ11 ነጥቦች ተቀምጦ የመጀመሪያውን ዙር የቋጨ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ተጠናክሮ ለመቅረብ ቀደም ካለው አሰልጣኝ ጋር የተለያየ ሲሆን በምትኩም አስራት አባተን አሰልጣኝ ስለማድረጉ ታውቋል። የቀድሞው የደደቢት ሴት ቡድን ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ ቡታጅራ ከተማ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት እና ካለፈው ዓመት ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝነት ቆይታን በማድረግ በመጨረሻም ከወራት በፊት ከክለቡ የተለያየው አሰልጣኙ ቀጣይ ማረፊያው የቀድሞው ክለቡ ቢሾፍቱ ሆኗል።

ክለቡ ባለበት ክፍት ቦታም አምስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል። ወደ ኢራቁ ክለብ ካመራ በኋላ የእግር ኳስ ህይወቱን ለመቀጠል የከበደው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ፣ ንግድ ባንክ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልድያ ተከላካይ ቶክ ጀምስ ፣ በሐረር ቢራ ፣ አዳማ ከተማ ፣ አዲስ አበባ እና ስሑል ሽረ ተጫውቶ ያሳለፈው ተከላካዩ ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ ፣ በአጥቂ ቦታ ላይ በሀድያ ሆሳዕና ፣ ቡታጅራ ከተማ ፣ ይርጋጨፌ ቡና (ጌዲኦ ዲላ) ፣ ሀምበርቾ እና በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቡና የተጫወተው ድንቅነህ ከበደ ፣ በቡታጅራ ፣ አርባምንጭ እና ወልድያ የተጫወተው አጥቂው ኤርሚያስ ሰብሬ እና በወልድያ ከተማ የነበረው ግብ ጠባቂው እስራኤል አሌ የክለቡ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ሆነዋል።