ሪፖርት | ቸርነት ጉግሳ ቀዝቃዛውን ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ነብስ ዘርቶበት የጣና ሞገዶቹን አሸናፊ አድርጓል

ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ቀዝቃዛ ፉክክር ያስመለከተው ተጠባቂው የመቻል እና ባህር ዳር ጨዋታ በቸርነት ብቸኛ ግብ አሸናፊው ተለይቶበታል።

በምሽቱ መርሐግብር መቻል እና ባህር ዳር ከተማ ሲገናኙ መቻሎች በ16ኛው ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና 3ለ2 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ነስረዲን ኃይሉ ፣ ፍጹም ዓለሙ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ምንይሉ ወንድሙ በምንተስኖት አዳነ ፣ ስቴፈን ባዱ አኖርኬ ፣ ዮሐንስ መንግሥቱ እና ቺጂኦኬ ናምዲ ተተክተው ሲገቡ የጣና ሞገዶቹ በተመሳሳይ ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አለልኝ አዘነ እና ዓባይነህ ፌኖ ወጥተው በምትካቸው በረከት ጥጋቡ እና ፍሬው ሰለሞን ገብተዋል።

በቀዝቃዛ እና ነፋሻማ የዐየር ፀባይ መደረግ የጀመረው ተጠባቂው ጨዋታ እምብዛም የማጥቃት አጨዋወት ያልታየበት ነበር። ይልቁንም ቡድኖቹ ኳስን መቆጣጠር እና መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥተው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በሙከራ ረገድ ቀዳሚ የነበረው ሞገዱ በ3ኛው ደቂቃ ከወደ ቀኝ ካደላ ስፍራ በፍራኦል መንግስቱ የቅጣት ምት ቀዳሚ ለመሆን ጥሯል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያልቦዘኑት መቻሎች በ10ኛው ደቂቃ በጥሩ የኳስ ግንባታ ከሜዳቸው በመውጣት በምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት ጠንከር ያለ ሙከራ ሰንዝረዋል።

ጨዋታው በእንቅስቃሴ ረገድ የወረደ ባይሆንም እንደ ተጠበቀው ግን የበዙ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ማስመልከት ዘበት ሆኖበታል። ዘለግ ካሉ ደቂቃዎች ጥበቃ በኋላም ለግብ የቀረበ ሙከራ የተስተናገደው በ35ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም ሀብታሙ ታደሠ ውሀ ሰማያዊ ለባሾቹን በተከላካዮች መሀል ተገኝቶ በአንፃሩ ሻል ያለ ሙከራ አድርጎ መሪ ሊያደርጋቸው ነበር። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መቻሎች ሌላ ሙከራ አድርገዋል። በሙከራውም አቤል ነጋሽ ከቀኝ መስመር ከከነዓን የተቀበለውን ኳስ ሰብሮ በመግባት ወደ ጎል ልኳታል። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የመቻል የግብ ክልል አቅራቢያ የሰነበቱት ባህር ዳሮች ከቆመ ኳስ እና ከተሻጋሪ ኳስ የአሊዮንዚን መረብ ለመድፈር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

የሁለቱ ቡድኖች ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት በሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎም በስታዲየም የሚገኙ እንዲሁም በቴሌቪዥን መስኮት የሚከታተሉ ተመልካቾችን ስሜት ከፍ የሚያደርግ ሙከራ ማስመልከት አልቻለም። ቡድኖቹ የመከላከል ስራ ላይ ተጠምደው የታዩ ሲሆን ለማጥቃት ሲወጡም የተጨናገፈባቸው ኳስ ግብ ክልላቸው ሳይደርስ በፈጣን ሽግግር የግብ ዘባቸውን እየሸሸጉ ጨዋታውን ቀጥለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቀዳሚው ሙከራ እንደ ተጠበቀው በአጥቂዎች ሳይሆን በጨዋታው ዋነኛ ተዋንያን ከሆኑት ተከላካዮች በአንደኛው የተደረገ ነበር። በዚህም ፍሬዘር ካሣ ባልተጠበቀ ቦታ ከሳጥኑ መግቢያ ተገኝቶ አክርሮ መትቶ የነበረ ቢሆንም ዩጋንዳዊው ዘብ አሊዮንዚ በቀላሉ ተቆጣጥሮታል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሽመልስ በቀል ሙከራ ያደረገውን ፍሬዘር በግል ብቃቱ ቀንሶት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ለመቻል ፈጥሯል።

በአንፃራዊነት በተሻለ ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክሩ የነበሩት ባህር ዳሮች ጨዋታው ሊገባደድ ሰባት ደቂቃዎች ሲቀሩት በቸርነት ጉግሳ የግንባር ኳስ መሪ ሆነዋል። ተከታታይ ሽንፈት ለማስተናገድ የተቃረቡት መቻሎች በ90ኛው ደቂቃ ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቡት ያሬድ አማካኝነት አቻ የሚሆኑበትን ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ቡድኑ ከያሬድ ሙከራ በተጨማሪም በላይኛው ሜዳ በመቆየት ሌሎች ጥቃቶችን ለማድረግ ቢጥርም ውጥኑ ሳይሰምርለት ቀርቷል። ጨዋታውም በባህር ዳር አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ የባህር ዳሩ አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እንደ ቡድን የነበሩበት የውጤት ጫና ነገሮችን እንዳከበደባቸው አመላክተው ጨዋታው እስኪጠናቀቅ ጊዜ ድረስ ተጫዋቾቻቸው ለከፈሉት መስዋትነት ምስጋና እና አድናቆት በማቅረብ የዛሬውን ውጤት እስከዛሬ በውጤት ላስከፏቸው ደጋፊዎች እንደሚያበረክቱት ተናግረዋል። የመቻሉ መሪ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው የቡድናቸው እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር ገልፀው ከትኩረት ማነስ የተነሳ ግቡ እንደተቆጠረባቸው ጠቁመው ቡድናቸው በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ እየተቀዛቀዘ የሚገኘው ከልምምድ ፕሮግራም አወጣት ጋር የተገናኘ እንደሆነ አብራርተዋል።