ሪፖርት | ኃይቆቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

በሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ 3ለ1 በሆነ ውጤት ሻሸመኔ ከተማን ረቷል።

የ17ኛ ሳምንት ቀዳሚ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማን ከሻሸመኔ ከተማ ሲያገናኝ ኃይቆቹ በ16ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲሣይ ጋቾ ፣ ኢዮብ ዓለማየሁ እና ዓሊ ሱሌይማን በመድኃኔ ብርሃኔ ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና ቸርነት አውሽ ተተክተው ሲገቡ በሻሸመኔ በኩል በተመሳሳይ ሳምንት ወላይታ ድቻን 2ለ1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ አሸብር ውሮን አስወጥተው ከኢትዮጵያ ቡና በውሰት ያስፈረሙትን ገዛኸኝ ደሳለኝ ተክተዋል።


10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ዓባይነህ ሙላት መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ወደ ጎል ቶሎ ቶሎ የመድረስ ፍላጎት በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ሻሸመኔዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት በገዛኸኝ ደሳለኝ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወት የቻሉት ኃይቆቹ  የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራቸውን 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ዓሊ ሱሌይማን ግብ ጠባቂውን አቤል ማሞን አታልሎ በማለፍ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ያደረገውን ሙከራ ትክክለኛ ቦታ ላይ የተገኘው ምንተስኖት ከበደ በጭንቅላቱ በመግጨት መልሶበታል።

የጨዋታው የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድል 22ኛው ደቂቃ ላይ በሻሸመኔዎች አማካኝነት ሲፈጠር ከቀኝ መስመር የተነሳውን ኳስ ማይክል ኔልሰን ከሲሣይ ጋቾ ጋር ታግሎ ከጨረፈው በኋላ ያገኘው አሸናፊ ጥሩነህ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ይዞበታል።

በቁጥር በመብዛት በተደጋጋሚ የተጋጣሚን ሳጥን መፈተን የቀጠሉት ሀዋሳ ከተማዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዓሊ ሱሌይማን ከተባረክ ሔፋሞ በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ቢመልስበትም የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ አግኝቶት በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮታል። ኃይቆቹ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ተመሳሳይ የግብ ዕድል ፈጥረው ዓሊ ሱሌይማን ከተባረክ ሔፋሞ በተቀበለው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ በእግሩ መልሶበታል።

የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት እና ተደራጅቶ ለመጫወት የተቸገሩት ሻሸመኔ ከተማዎች አማካያቸው ሀብታሙ ንጉሤ ከአምስት የሀዋሳ ተጫዋቾች ጋር ተፋጥጦ ያቋረጠባቸው ድንቅ ኳስ ቢታደጋቸውም አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ሁለት ደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። አማኑኤል ጎበና በጥሩ ዕይታ የሰነጠቀለትን ኳስ የተቆጣጠረው ዓሊ ሱሌይማን ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በአስደናቂ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ድንቅ አጀማመር ያደረጉት ሻሸመኔዎች የግብ ዕድሎችን በተደጋጋሚ በመፍጠር የተጋጣሚያቸውን ሳጥን መፈተን ሲችሉ 51ኛው ደቂቃ ላይም ጌትነት ተስፋዬ ያመቻቸለትን ኳስ አሸናፊ ጥሩነህ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ሲያስወጣበት ያንኑ ኳስ ከማዕዘን ተሻምቶ ከተመለሰ በኋላ ያገኘው ገዛኸኝ ደሳለኝም ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በድጋሚ መልሶበታል።


ሻሸመኔ ከተማዎች በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በፈጣን ሽግግር በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወታቸውን ቀጥለው 55ኛው ደቂቃ ላይ በምንተስኖት ከበደ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ የነበረው ማይክል ኔልሰን የግብ ጠባቂውን ጽዮን መርዕድን እንቅስቃሴ በማስተጓጎሉ ግቡ ሊሻር ችሏል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም አሸናፊ ጥሩነህ ከጌትነት ተስፋዬ እና ከገዛኸኝ ደሳለኝ በተመቻቹለት ኳሶች ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ ነበር።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ጨዋታውን ለማረጋጋት ጥረት ያደረጉት ሀዋሳዎች በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራቸውን 71ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ተባረክ ሄፋሞ ከታፈሰ ሰለሞን በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው 81ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሻሸመኔዎች ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው አሸብር ውሮ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ስንታየሁ መንግሥቱ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ሀዋሳዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመጠኑ ግለታቸውን በመጨመር በዓሊ ሱሌይማን አማካኝነት ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ፈጣኑ አጥቂ 86ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ የግሩ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ሲያስወጣበት 89ኛው ደቂቃ ላይ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ደግሞ በቀኙ ቋሚ ለጥቂት ወጥቶበታል።

በተጨመሩ 8 የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ሦስተኛው ደቂቃ ላይ ኃይቆቹ ሦስተኛ ግብ አስቆጥረዋል። ተባረክ ሄፋሞ ያመቻቸለትን ኳስ ከቀናት በፊት ለቡድኑ የፈረመው እና ተቀይሮ የገባው አጥቂ እስራኤል እሸቱ በጥሩ አጨራረስ ግብ አድርጎታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ሻሸመኔዎች በስንታየሁ መንግሥቱ አማካኝነት ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ሲመለስባቸው 90+7ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የሀዋሳው ዓሊ ሱሌይማን ያደረገውን ሙከራ አቤል ማሞ አግዶበታል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ በመጀመሪያው አጋማሽ መሃል ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው እና በሁለተኛው አጋማሽ ግን እንደተሻሻሉ ሲጠቁሙ የተከላካይ አማካዩ ለተከላካዮች ሽፋን መስጠት ላይ ክፍተት እንደነበረበት በመናገር “የመጀመሪያው ጎል ከጨዋታው ውጪ ነበር በረዳት ዳኛው ስህተት ተቆጥሮብናል” ሲሉም ኮንነዋል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ከፈጠሩት የግብ ዕድል ብዛት አንጻር ያስቆጠሩት ግብ እንደሚያንስ በመናገር የአጥቂዎቻቸውን ፍጥነት መሠረት ያደረገ የማጥቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚጫወቱ በመግለጽ የአዲሱ ፈራሚያቸው እስራኤል እሸቱ እንቅስቃሴም እንዳስደሰታቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።