ዋልያዎቹ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሊያደርጉ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሳምንታት በኋላ በሜዳው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ሊያደርግ ነው። ተጋጣሚውም በትናንትናው ዕለት ዝግጅት ጀምራለች።

በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአንድ የጨዋታ ሳምንት በኋላ ሲቋረጥ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርግ ቀድሞ መነገሩ አይዘነጋም። ብሔራዊ ቡድኑ የቻን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ስለሌሉበት በዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ወቅት ራሱን ለመፈተሽ ሲጥር ቆይቶም በመጨረሻ ውጥኑ ፍሬ እንዳገኘ ይፋ ሆኗል።

ይህንን ተከትሎ መጋቢት 12 እና 15 ብሔራዊ ቡድኑ ከሌሴቶ አቻው ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደርጋል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከደቂቃዎች በፊት ይዞት በወጣው መረጃ ሁለቱም ጨዋታዎች በደጋፊው ፊት እንደሚደረጉ ቢያመላክትም በየትኛው ሜዳ እንደሚደረጉ ግን አልተጠቆመም።

ተጋጣሚው የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድንም ለጨዋታው የተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ከትናንት ጀምሮ መደበኛ ዝግጅት ማድረግ ጀምሯል።