ሪፖርት | አደገኛ ሙከራዎችን ማሳየት ያተሳነው የምሽቱ ጨዋታ ያለግብ ተቋጭቷል

ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት የሲዳማ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

በምሽቱ ጨዋታ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት መልስ ባደረጓቸው አምስት ለውጦች መኳንንት ካሳ ፣ ደግፌ ዓለሙ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ እና ዳመነ ደምሴን በደስታ ደሙ ፣ ብርሀኑ በቀለ ፣ ሙሉቀን አዲሱ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ቡልቻ ሹራ ተክተዋል። የወልቂጤው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በበኩላቸው በቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት የተጠቀሙበተን የተጨዋቾች ምርጫ ዳግም ይዘው ገብተዋል።

በሲዳማ ቡና የኳስ ቁጥጥር ወደ ሰራተኞቹ ሜዳ አድልቶ በጀመረው ጨዋታ ወልቂጤዎች በሂደት ኳስ መስርተው የመውጣት የበላይነቱን ተረክበዋል። በዚህም ቡድኑ ወደ ቀኝ ካደላ ማጥቃት እና ከማዕዘን ምት ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክሯል። በአንፃሩ ሲዳማዎች የተጋጣሚያቸውን የኳስ ቁጥጥር በማቋረጥ ፈጥነው ወደ ማጥቂያ ዞን ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። ከበዛብህ መለዮ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ደካማ የርቀት ሙከራዎች በኋላም ቡድኑ የጨዋታውን ቀዳሚ ከባድ ሙከራ 22ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርግ ቡልቻ ሹራ ከግራ መስመር የተላከለትን ኳስ ይዞ ሰብሮ ወደ ሳጥን በመግባት ተስፋዬ መላኩን አታሎ አክርሮ ቢመታም ንቁ የነበረው ፋሪስ አለዊ አድኖበታል።

እየተቀዛቀዘ በሄደው አጋማሽ በጉዳት ምክንያት ወንድምአገኝ ማዕረግን በመሳይ ጳውሎስ የተኩት ወልቂጤዎች የኳስ ቁጥጥራቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ አቅም እያጣ የግብ ሙከራ ሊያመጣላቸው ባይችልም የግብ ክልላቸውን በትኩረት ተከላክለዋል። ከቡልቻ ሹራ ሙከራ በኋላ ያለቀለት ዕድል ያልፈጠሩት ሲዳማዎች በተሻለ አስፈሪነት ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል የደረሱባቸው ቅፅበቶች ቢታዩም ጥረቶቻቸው የሰራተኞቹን የመከላከል ትጋት መስበር ሳይችል ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ የወልቂጤ ከተማ ኳስ ቁጥጥር ተዳክሞ የሲዳማ ቡና የማጥቃት ሽግግር ጎላ ብሎ ቢመለስም የግብ ሙከራዎችን ማየት ግን አዳጋች ሆኗል። ሲዳማዎች በቶሎ ኳሶችን ከመሀል አቋርጠው ወደ ግብ ክልል ቢቀርቡም ወልቂጤዎች በቶሎ ወደ መከላከል ቅርፃቸው በመመለስ ካባድ አደጋ እንዳይፈጠርባቸው ማድረግ ችለዋል። ከመከላከሉ ባለፈ ወልቂጤዎች የመጨረሻ የግብ ዕድል ባያገኙም በሂደት ወደ ሲዳማ የሜዳ ክልል በመግባት ከቆሙ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩም ተስተውሏል።

በይበልጥ ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ ወልቂጤ ከተማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የሲዳማ ቡናን የማጥቃት ጥረቶች በማርገብ ከኳስ ውጪም ጥሩ የመከላከል ሽግግርን በመተግበር ጨዋታውን ተቆጣጥረው ዘልቀዋል። ይልቁኑም ከርቀት ከሚገኙ የቆሙ ኳሶች ከሲዳማ ቡና በንፅፅር የተሻለ ጫና መፍጠር ችለው ነበር። በሌላ ጎን ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር የሲዳማ ቡና የማጥቃት አማራጮች የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ብቻም ሳይሆን ወደ ወልቂጤ ሳጥን በመቅረብም ጭምር ደካማ ሆነው ታይተዋል።

ሙከራ የራበው የምሽቱ ጨዋታ በአራተኛው ጭማሪ ደቂቃ ተመስገን በጅሮንድ ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ መግቢያ ላይ አክርሮ በመታው እና መክብብ ደገፉ በቅልጥፍና ባወጣው ድንገተኛ ሙከራ ነፍስ ዘርቶ ቢታይም ጎል ለማሳየት ሳይታደል 0-0 ተጠናቋል።

 

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በእንቅስቃሴ ከዕረፍት መልስ ራሳቸውን ማግኘታቸውን አንስተው ውጤቱ ለቀጣይ ጨዋታዎች መነሻ እንደሚሆን በመጠቆም ቡድናቸው የተሻለ ስብስብ እና ልምድ ያለው አሰልጣኝ ከያዘ ቡድን ጋር ባደረገው ፉክክር ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸው በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ መገደባቸው እና የግብ ዕድል አለመፍጠራቸውን አምነው መነሻውም ከውጤት መራቅ የመጣ ጫና መሆኑን አንስተዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ቡድናቸው የፊት መስመር አጥቂ በመፈለግ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።