መረጃዎች| 68ኛ የጨዋታ ቀን

የአስራ ሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ይቀጥላሉ ፤ በሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች አንደሚከተለው ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ፋሲል ከነማ

በዝውውሩ ንቁ ተፋትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙ መድኖችና ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ የሚገቡት ዐፄዎቹ የሚያገናኘውን ጨዋታ 10:00 ሲል ይጀምራል።

አስራ ሦስት ነጥቦች በመሰብሰብ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ከፍ ብለው የሚገኙት መድኖች ከአደገኛው ክልል ለመራቅ ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። መድኖች ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው በመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች አቻ በመለያየት ውስን መሻሻሎች ቢያሳዩም አሁንም የግብ ማስቆጠር ችግራቸውን መቅረፍ አልቻሉም። ቡድኑ ካለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሦስቱ ግብ ሳያስቆጥር መውጣቱም የችግሩ ማሳያ ነው። በዝውውር መስኮሩ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ተጫዋቾች አስፈርመው በጥልቀትም በጥራትም ውስን የነበረው አማራጫቸው ማስፋት የቻሉት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በነገው ጨዋታ በርካታ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል። ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ መሀል ሀይደር ሸረፋና አናንያ ጌታቸው በጨዋታው ተሳትፎ ይኖራቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።

በሀያ ስድስት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ዐፄዎቹ ወደ ሊጉ አናት የሚያስጠጋቸውን ነጥብ ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ፋሲል ከነማዎች ከሁለት ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ከመመራት ተነስተው ሀዋሳ ከተማን በማሸነፍ ወደ ድል አድራጊነት ተመልሰዋል። ሆኖም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በውጤት ረገድ የታየባቸውን የወጥነት ችግር መቅረፍ ይኖርባቸዋል። ቡድኑ ከጣፋጩ የመጨረሻ ሳምንት ድል በፊት ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ሽንፈት፣ ሁለት አቻና አንድ ድል ማስመዝገቡ የወጥነት ችግሩ ማሳያ ነው። ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የማጥቃት አጨዋወታቸውም በጊዜ ሂደት በጎ ለውጦች ታይቶበታል። ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ሦስት ለባዶ ካሸነፈበት የዘጠነኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ቢያስቆጥርም ከዛ በኋላ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ግን ሰባት ግቦች በማስቆጠር በጥሩ የመሻሻል ሂደት ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ መካከል ሀይደር ሸረፋ እና አናንያ ጌታቸው ለነገው ጨዋታ የሚደርሱ ሲሆን ተክለማርያም ሻንቆ በቀሪ የወረቀት ሥራዎች ነገ እንደማይኖር ተረጋግጧል። ከሰሞኑ ቡድኑን ስለመቀላቀሉ የተነገረለት የአጥቂው አብዲሳ ጀማል ዝውውርም የተወሰነ እክል እንደገጠመው ታውቋል። ዐፄዎቹ በነገው ጨዋታ በጉዳይም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው መድን አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ ሦስቱ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። መድን ሁለት ጎል ሲያስቆጥር ፋሲል አንድ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ዳንኤል ግርማይ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወይንሸት አበራ እና ዘሪሁን ኪዳኔ ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀምበርቾ

በእጃቸውን የገባውን ደረጃ የማሻሻል ዕድል ለመጠቀም ወደ ሜዳ የሚገቡት ፈረሰኞቹ ከሀምበርቾ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ምሽት ላይ ይከናወናል።

በሰላሣ አንድ ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ በሁለተኛነት የተቀመጠውን መቻል ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል አግኝተዋል። ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው መሪዎቹን እግር በእግር መከታተላቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በድሬዳዋ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ወዲህ በብዙ መለክያዎች መሻሻሎች አሳይተዋል። ከሽንፈቱ ወዲህ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሦስቱ አሸንፎ አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱና አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ ቡድኑ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት እንዳለ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስቆጠረው የቡድኑ ማጥቃት አጨዋወት ቀላል ፈተና አይጠብቀውም። ቡድኑ ጠጣርና መከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት የሚመርጥ ቡድን እንደመግጠሙ ዕድሎች የመጠቀም ክፍተቱን ቀርፎ መቅረብ ይኖርበታል።

ሰባት ነጥቦች ሰብስበው በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት ሀምበርቾዎች በሊጉ የመትረፍ ዕድላቸውም ለማስፋት ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሳይጠበቁ ከወሳኙ የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው ከወጡ በኋላ ባደረጉት የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ የእንድ ለባዶ ሽንፈት ያስተናገዱት ሀምበርቾዎች ከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ችግር አለባቸው። ከአዳማ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ከተለያየበት የሦስተኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው አስራ ሦስት ጨዋታዎች ውስጥ በአስራ ሁለቱ ግብ ሳያስቆጥር የወጣው ቡድኑ በተጠቁሱት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን ሁለት ብቻ ነው። በነገው ጨዋታም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው ለበርካታ ሳምንታት ኳስና መረብ ያላገናኘው የፊት መስመራቸው ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጉዳት ላይ ያለው የመስመር ተጫዋቹ ተገኑ ተሾመ በጨዋታው አይሰለፍም በአንፃሩ ሀምበርቾዎች በጉዳት ይሁን በቅጣት የሚያጠት ተጫዋች የለም፤ ሆኖም ክለቡ በርከት ካሉ ተጫዋቾች ጋር በመለያየት ላይ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮ የውድድር ዘመን ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሲያሸንፍ በኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ተገናኝተው በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸንፏል።

ሔኖክ አክሊሉ በዋና ዳኝነት አስቻለው ወርቁ እና እያሱ ካሳሁን ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በአንፃሩ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።