አቡበከር ሳኒ ወደ አዲስ ክለብ አምርቷል

ባለፉት ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ቆይታ የነበረው የመስመር አጥቂ አሁን ላይ ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ ማምራቱ ተረጋግጧል።

በዝውውር መስኮቱ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስና የወልቂጤ ከተማ ተጫዋች የሆነው አቡበከር ሳኒን በማስፈረም በዝውውር መስኮቱ ያዘዋወሯቸው የተጫዋቾች ቁጥር አምስት አድርሰዋል።

ቀደም ብለው ሀይደር ሸረፋ ፣ አናንያ ጌታቸው፣ ሚልዮን ሰለሞን፣ ተክለማርያም ሻንቆና ያስፈረሙት መድኖች በመጀመርያው ዙር ደካማ የነበረውን የፊት መስመራቸው ለማጠናከር በማለም ከወልቂጤ ጋር የነበረውን ቀሪ ውል በስምምነት ያቋረጠውን አቡበከር ሳኒን የግላቸው ማድረጋቸው ሲታወቅ አቡበከርም በቀጣይ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የሚያቆይ ውል ከአዲሱ ቡድኑ ጋር አስሯል።

በአንፃሩ ከቀናት በፊት ከአዳማ ከተማ መድንን ለመቀላቀል ስምምነት ፈፅሞ የነበረው አብዲሳ ጀማል የዝውውር ሂደት ግን እክል እንደገጠመው ለማወቅ ችለናል።