ሪፖርት | እጅግ አስገራሚው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ሁለት ቀይ ካርዶች በተመዘዙበት ጨዋታ ሁለት የፍጹም ቅጣት ምቶችን ያመከኑት አዳማዎች በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከወላይታ ድቻ ጋር 1ለ1 ተለያይተዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ አዳማዎች በ16ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በሱራፌል ዐዎል እና ከቡድኑ ጋር በማይገኘው ቻርለስ ሪባኑ ምትክ ታዬ ጋሻውን እና አድናን ረሻድን ሲተኩ በተመሳሳይ ሳምንት በሻሸመኔ ከተማ 2ለ1 በተሸነፉት የጦና ንቦቹ በኩል በተደረገ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥም በውድድር የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው መልካሙ ቦጋለ ፣ አናጋው ባደግ እና መሳይ ኒኮል በአንተነህ ጉግሳ ፣ ፍጹም ግርማ እና አብነት ደምሴ ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብተዋል።

10 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ገና በ4ኛው ደቂቃ ብሥራት በቀለ ከግራ መስመር አሻምቶት ዘላለም አባተ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ በሞከረው እና ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ በመለሰበት ኳስ ጫናቸውን የጀመሩት ድቻዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀመረዋል። ብዙዓየሁ ሰይፉ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ አሻግሮት አበባየሁ ሀጂሶ በትክክል ሳይመታው ቀርቶ የተቆረጠውን ኳስ ያገኘው ብሥራት በቀለ ማስቆጠር ችሏል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ እና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት አዳማዎች 17ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ሲያደርጉ ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ብዙ ሳይቸገር መልሶበታል። በተመለሰው ኳስም ወላይታ ድቻዎች ወርቃማ የግብ ዕድል አግኝተው ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ለብቻው ሆኖ የተቆጣጠረው ዘላለም አባተ እጅግ ደካማ በሆነ ውሳኔ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

አዳማዎች ቀስ በቀስ ጫና በመፍጠር በቢኒያም ዐይተን አማካኝነት የግቡን የግራ ቋሚ የገጨች ሙከራ ካደረጉ በኋላ 33ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሚሆኑበት እጅግ ወርቃማ ዕድል አግኝተው ቢኒያም ዐይተን በግሩም ክህሎት አታልሎ ወደ ሳጥን ሲገባ መሳይ ኒኮል ጥፋት ሠርቶበት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ መሬት ለመሬት በግራ በኩል ቢመታውም ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ተቆጣጥሮታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ወላይታ ድቻዎች ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገው ዘላለም አባተ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሥራት በቀለ በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ጨዋታው 45ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ትኩረት የሚስብ ክስተት ተፈጥሯል። የወላይታ ድቻው ወሳኝ አጥቂ እና የወድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቢኒያም ፍቅሩ እና የአዳማ ከተማው አማካይ አድናን ረሻድ በፈጠሩት ሰጣ ገባ በዋና ዳኛው ኢያሱ ፈንቴ ውሳኔ በቀይ ካርድ ተሰናብተዋል። ሆኖም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የአዳማው ቦና ዓሊ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ግሩም ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 51ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው የግብ ዕድል ተፈጥሮ ብሥራት በቀለ ከሳጥን አጠገብ ያገኘውን ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም ዒላማውን ሳይጠብቅ ሲወጣበት 57ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ አስገራሚ ክስተት ተፈጥሯል። ናትናኤል ናሴሮ በቢኒያም ዐይተን ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ ከመጀመሪያው በተቃራኒ በቀኝ በኩል ቢመታውም ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በድጋሚ አድኖበታል።

አዳማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቢገቡም የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን የተሻሉ  የነበሩት ድቻዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ በዘላለም አባተ 71ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በብሥራት በቀለ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ከሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች አኳያ በየ ጨዋታው የሚታየው አባካኝነታቸው ዛሬም ጎልቶ የታየባቸው የጦና ንቦቹ 78ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ዘላለም አባተ በሳጥን የቀኝ ክፍል ይዞት በመግባት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ኢዮብ ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ ከመሬት በማንጠር ያደረገውን ሙከራ የአዳማው ተከላካይ ሳዲቅ ዳሪ በግንባር ገጭቶ መልሶበታል።

እየተቀዛቀዘ በሄደው እና ሁለቱም ቡድኖች መጠነኛ ፉክክር ባደረጉባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች 90ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ሀጂሶ ከሳጥን አጠገብ ሞክሮት በግቡ የቀኝ ቋሚ ከወጣው ኳስ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ የተጨመሩ 6 ደቂቃዎች ቢያልቁም 90+7ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ሙሴ ኪሮስ ከግራ መስመር የተነሳውን ኳስ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮት ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ተጫዋቾቻቸው ሰዓት አልቋል በሚል መዘናጋት በሠሩት ስህተት ግብ ማስተናገዳቸውን በመናገር የግብ ዕድሎችን የሚያባክኑት አጥቂዎቻቸው ከልምድ ማነስ የተነሳ መሆኑን በመጠቆም የቢኒያም ፍቅሩ በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገድ ክፍተት እንደሚፈጥርባቸው ሀሳባቸውን ሲሰጡ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው በመጀመሪያ ደቂቃዎች የሚያስተናግዷቸው ግቦች ውጤት እንዲያጡ ምክንያት እንደሆኑባቸው በመግለጽ ሁለት የፍጹም ቅጣት ምቶችን ያባከነው ዮሴፍ ታረቀኝ የቡድናቸው ወሳኝ ተጫዋች እንደሆነ በመጠቆም “ሦስተኛ ብናገኝም እሱን ነበር የምናስመታው” ሲሉ የጣሉበትን እምነት አበክረው ሲያስታውቁ ቀይ ካርድ የተሰጣቸው ተጫዋቾች በምክር ቢታለፉ የተሻለ እንደነበር ገልጸዋል።