ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አስራተ አባተ አዲሱን ስራውን በድል ጀምሯል

በምድብ “ለ” የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ቢሾፍቱ ከተማ ፣ ደሴ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል።

ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የሁለተኛ ዙር የመክፈቻ መርሃግብር ቢሾፍቱ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን የረታበት ነበር።

የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ቢሾፍቱ ከተማዎች የተሻሉ በነበረበት የመጀመሪያው አጋማሽ በ14ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘውን ኳስ ዘካሪያስ ከበደ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ቢመለስበትም በ22ኛው ደቂቃ በድጋሚ በፈጣን ሽግግር ወደ አዲስ ከተማ የግብ ክልል በመግባት አብዱላዚዝ ኡመር የግል ብቃቱን በመጠቀም ግሩም ግብን በማስቆጠር ቡድኑን መሪ በማድረግ ነበር አጋማሹን በበላይነት የፈፀሙት።

የሁለተኛው አጋማሽ አጀማመርም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ የቀዘቀዘ እና ብዙም የግብ ሙከራ ያልተመለከትንበት አጋማሽ የነበረ ሲሆን በዚህም አልፎ አልፎ አዲስ ከተማ የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ቢያረጉም የቢሾፍቱ ከተማ የተከላካይ እና የአማካይ ስፍራ ጠንካራ በመሆኑ ግልፅ የግብ እድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

በአንፃሩ ቢሾፍቱ ከተማ የሚያገኟቸውን ኳሶች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ግብ ለማድረስ ሲጥሩ ተስውሏል ይህንን ተከትሎ በ82ኛው ደቂቃ በቢሾፍቱ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ትንሳኤ አየለ ከዘካሪያስ ከበደ ጋር በመቀባበል ያገኘውን ኳስ የአዲስ ከተማ ግብ ጠባቂ ምንም ማድረግ በማይችልበት ሁኔታ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ አዲስ ከተማ በቀሩት ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ተስፈኛው ተጫዋች ተካልኝ አስፋው ከርቀት በአስገራሚ ሁኔታ ያስቆጠረ ቢሆንም ቡድኑን ከሽንፈት መታደግ ሳይችል ቀርቷል በዚህም ጨዋታው አስራት አባተን ዳግም በሀላፊነት በሾሙት ቢሾፍቱ ከተማዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 8:00 ላይ በተደረገው መርሀግብር የካ ክፍለ ከተማን ከደሴ ከተማ ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውም በደሴ ከተማ አሸናፊነት ተደምድሟል።

ደሴ ከተማ በፈጣን ቅብብሎች ሆነ ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን በመድረስ ረገድ የተሻሉ በነበሩት የመጀመሪያው አጋማሽ መሪ ለመሆን የፈጀባቸው 5 ደቂቃ ነበር ፤ ጫና በመፍጠር ያገኙትን ኳስ አንዋር መሀመድ ወደ የካ ሳጥን ይዞ ለመግባት ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ በተሰራበት ጥፋት መነሻነት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በሱፍቃድ ነጋሽ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

መሪ ከሆኑ በኃላ ይበልጥ ጫና ለመፍጠር የሞከሩት ደሴዎች በ14ኛው ደቂቃ አቡሽ ደርቤ ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን አሳድገዋል።

ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኃላ በተወሰነ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት የካ ክፍለከተማዎች ጥረታቸው በ41ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል ፤ ከማዕፈን የተሻማን ኳስ ተጠቅሞ ጃኔክስ አወቀ በማስቆጠር ለቡድኑ ተስፋን ፈንጥቋል።

በጥንቃቄ የተሞላ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ደሴዎች ረዘም ላለ ጊዜ ከኳስ ጋር ሲያሳልፉ በአንፃሩ የካዎች ደግሞ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው በደሴ ከተማዎች የ2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የዕለቱ የማሳረጊያ መርሃግብር በነበረው ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ ከፋ ቡናን ያሸነፈበት ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ እና ፍጥነት የታየበት ጨዋታ ነበር።

በመጀመሪያ ዙር ለስልጤ ወራቤ ጥሩ ግልጋሎት ሲያደርግ የነበረው ማትያስ ኤሊያስ በሁለተኛው ዙር የጋሞ ጨንቻን የፊት መስመር በመምራት የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገበት በዚህ ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል።

ካፋ ቡና ኳስን በረጃጅሙ በመላክ የግብ እድል ለመፍጠር የጣሩ ሲሆን በ10ኛው ደቂቃ ከካፋ ቡና የግብ ክልል የቀኝ ክፍል የተሻገረውን ኳስ ማትያስ ኤሊያስ በመዘናጋት ሳቢያ ንጋቱ ፀጋዬ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ካፋ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመሄድ የግብ እድል ለመፍጠር ቢጥሩም ጠንካራውን የጋሞ ጨንቻ የተከላካይ ክፍል ማስከፈት ተስኗቸው ግብ ሳያስቆጥሩ አጋማሹ በጋሞ ጨንቻ መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከፋ ቡና የተወሰደበትን የግብ ብልጫ ለመቀልበስ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም በ65ኛው ደቂቃ ጋሞ ጨንቻ በጥሩ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ጌታሁን ገዛኸኝ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል። በቀሪ ደቂቃዎችም ካፋ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢሞክርም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በጋሞ ጨንቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።