ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ንብ ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ዙር በዛሬው እለት ጅማሮውን ሲያደርግ በምድብ ሀ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ንቦችነጥብ ሲጥሉ ጅማ አባ ጅፋር ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አሳክቷል።

የምድቡ የመክፈቻ በነበረው መርሃግብር ረፋድ ሶስት ላይ ወልዲያን ከጅማ አባ ጅፋር ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውንም ጅማ አባ ጅፋሮች ድል ያደረጉበት ነበር።

ወልዲያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ሆነ በጥቅል እንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በዚህም በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ሳጥንም የደረሱበት ነበር ፤ ሆኖም የፈጠሯቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጅማ አባጅፋር በአንፃሩ በብዙ መመዘኛዎች ቢበለጡም የፈጠሯቸውን ውስን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት ለመቀየር የጣሩበት ነበር ፤ በ23ኛው ደቂቃ ማዕዘን ምት የፈጠሩትን አጋጣሚ ተመስገን አማረ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠራት ግብ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ወልዲያዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ኳስን ይዘው ወደፊት ገፍተው ቢጫወቱም የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የጅማ አባ ጅፋሩ የግብ ዘብ ዮሀንስ በዛብህ የሚቀመስ አልሆነም።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ጅማ አባጅፋሮችም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሙከራ ያደረጉ ሲሆን አጋማሹ ጥሩ ፉክክርን የተመለከትንበት ነበር።

ሆኖም ግን ጨዋታ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን በጅማ አባጅፋሮች 1-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

በዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ በተካሄደው የ10 ሰዓቱ መርሃግብር ቤንች ማጂ ቡና ከንብ ጋር ያገናኘው ጨዋታ በነጥብ መጋራት የተደመደመ ነበር።

ገና ከጅምሩ ግብ ባስተናገደው ጨዋታ በ2ኛው ደቂቄ ንቦች መሪ መሆን ችለዋል ፤ በቅብብል ተጋጣሚ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ እዮብ ደረሰ አስቆጥሮ ንብን መሪ አድርጓል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በረጃጅም ኳሶች ወደፊት ሲደርሱ የተስተዋሉት አቦሎቹ በ14ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ እንዳልማው ድክሬ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ጨዋታው አንድ አቻ እንዲሆን አስገድዷል።

ጨዋታ በአቻ ውጤት በቀጠለበት ሁኔታ አቻ በ35ኛው ደቂቃ  በሀዋሳ በጣለው ንፋስ አዘል ዝናብ መነሻነት ጨዋታው ለ11 ያክል ደቂቃ ሊቋረጥ ችሏል።

ከተቋረጠ በኋላ ድጋሚ ወደሜዳ የተመለሱ ሁለቱ ቡድኖች ማራኪ ጨዋታ ለተመልካች አሳይተዋል።ሆኖም ግን ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ የተስተዋለ ሲሆን አጋማሹን በአቻ ውጤት ፈፅመዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ግብ ለማስቆጠር ንቦች በኳስ ቁጥጥር በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት አስፈሪ ዕድሎችን የፈጠሩት ቤንች ማጂ ቡናዎችም ጥረት ቢያደርጉም ውጤቱን ሊቀይር የሚችል ግብ ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።