መረጃዎች | 69ኛ የጨዋታ ቀን

የአስራ ሰባተኛ ሳምንት መገባደጃ የሆኑት ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ያስቆጠሩ ንግድ ባንኮች ጥቂት ግቦች ካስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች የሚያደርጉት የዕለቱ ተጠባቂ መርሃግብር ቀን 10 ሰዓት ላይ ጅማሮውን ያደርጋል።

በሀያ ሁለት ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የነገው ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ሁለት ደረጃዎች ማሻሻል ይችላሉ። በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ አልመው ወደ ሜዳ የሚገቡት ሀድያዎች በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ መቻል ላይ ሦስት ግቦች በማስቆጠር አሸንፈው እንደ መምጣታቸው እና ለአስራ አራት ሳምንታት በዘለቀው ያለመሸነፍ ጉዞ ውስጥ መሆናቸው በነገው ጨዋታ ትልቅ ግምት እንዲሰጣቸው ያደርጋል።

የግብ ማስቆጠር ችግር ያለበት ቡድኑ ፤ በውድድር ዓመቱ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻለው በሦስት አጋጣሚዎች ብቻ ነው ቢሆኖም በተቃራኒው ደግሞ የሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀትም ባለቤት ነው። በነገው ጨዋታም በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ካስቆጠረው የንግድ ባንክ የፊት መስመር የሚያደርጉት ፍጥጫ ተጠባቂ ነው።

ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ንግድ ባንኮች የነጥብ ልዩነቱን የሚያሰፉበት ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል። ሀምራዊ ለባሾቹ ከሁለት ተከታታይ ነጥብ መጣሎች አገግመው ወደ ጥሩ ብቃት ተመልሰዋል፤ ከዛ በዘለለም በተሸነፉባቸው ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማምረት ተስኖት የነበረው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት አስደናቂ ለውጥ አምጥቷል።

ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስቆጠር ሲችል በእንቅስቃሴ ረገድም መሻሻሎች አሳይቷል። በነገው ጨዋታም የሊጉ ጠንካራ የመከላከል ክፍል ካለው ጠጣር ቡድን እንደመግጠማቸው የፊት መስመራቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ብሩክ እንዳለ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም።

በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ሁሉንም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸንፎ 4 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕና ምንም ጎል ማስቆጠር አልቻለም። በኢትዮጵያ ዋንጫ ግን ዘንድሮ ሁለተኛ
ዙር ላይ ተገናኝተው ሀድያ ሆሳዕና 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል።


ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሁለት በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙ ቡድኖች የሚያገናኝው የምሽቱ ጨዋታ ብዙዎች በትኩረት የሚጠብቁት ነው።

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ግስጋሴያቸውን ለማስቀጠልና ወደ መሪዎች ይበልጥ ለመጠጋት ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ። በመጀመርያው ዙር መገባደኛ ላይ በአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ስር ለመጀመርያ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥሩ ከወጡ በኋላ ወደ ቀደመው ብቃታቸው ለመመለስ ጊዜ ያልፈጀባቸው ቡናማዎቹ ሲዳማ ቡናን በገጠሙበት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ሦስት ግቦች በማስቆጠር በአምስት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት የግብ መጠን አስራ አንድ አድርሰዋል።

በሀያ ሁለት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸው ለማሳካትና ደረጃቸውን ለማሻሻል ለቡናማዎቹን ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑ ይገመታል። ብርቱካናማዎቹ የነገውን ጨዋታ ካሸነፉ ሦስት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል አላቸው፤ ይህንን ተከትሎም ከፍ ባለ የማሸነፍ ስነ-ልቦና ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ቡድኑ ምንም እንኳ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ብቻ አስተናግዶ ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት መገንባት ቢችልም በተቃራኒው በቂ ግቦችን በማስቆጠር ላይ ግን አይገኝም።
በነገው ጨዋታም በከፍተኛ የተደጋፊ ቁጥር ታጅበው በተከታታይ ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን ስለሚገጥሙ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጫላ ተሺታ እና መሐመድኑር ናስር ነገም በጉዳት የማይኖሩ ተጫዋቾች ናቸው።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ተመስገን ደረስና አብዱልፈታህ ዓሊ በጉዳት፤ ኤልያስ አህመድ ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ ተሳትፎ አይኖራቸውም። በቤተሰብ ጉዳይ ከቡድኑ ጋር የሌለው ዳዊት እስጢፋኖስም በነገው ጨዋታ አይኖርም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 23 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 14 በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ይዟል። አምስት ጨዋታ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ድሬዳዋ 4 ጨዋታ አሸንፏል። ቡናማዎቹ 41፣ ብርቱካናማዎቹ 22 ጎሎች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)