ሪፖርት | ንግድ ባንክ መሪነቱን ማጠናከር የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል

ተጠባቂው የሀዲያ ሆሳዕና እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተገናኝተው ንግድ ባንኮች በ16ኛው ሳምንት አዳማ ከተማን 4ለ1 ያሸነፉበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ነብሮቹ በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት መቻልን 3ለ2 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ታፔ አልዛየር በያሬድ በቀለ መስመር ላይ ተመስገን ብርሃኑ በሠመረ ሀፍተይ ተተክተው ገብተዋል።

10፡00 ላይ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑኄ ወልደጻድቅ የፊሽካ ድምፅ ለተመልካች ሳቢ ፉክክር እያስመለከተ በተጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በተሻለ ግለት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ 7ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያው ተመስገን ብርሃኑ ከብሩክ ማርቆስ በተሰነጠቀለት ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ መሬት ለመሬት መትቶት ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን የያዘበት ኳስ የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።

በኳስ ቁጥጥሩ ንግድ ባንኮች ብልጫውን መውሰድ ቢችሉም በመልሶ ማጥቃቱ የተሻሉ የነበሩት ነብሮቹ 17ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አስወጥቶበታል። ባንኮቹ በአንጻሩ መዳረሻቸውን ቢኒያም ጌታቸው ላይ ባደረጉ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።

እንደ አጀማመሩ መቀጠል ያልቻለው ፉክክር በመጠኑ እየተቀዛቀዘ ሄዶ በሚቆራረጡ ኳሶች ሲታጀብ ንግድ ባንኮች 41ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ጌታቸው 45ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሱሌይማን ሀሚድ በኪቲካ ጅማ ተመቻችሎት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታውን በጥሩ እንቅስቃሴ የጀመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 51ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው አዲስ ግደይ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ጌታቸው ኳሱን በማመቻቸት እና ተገልብጦ በመምጣት ያደረገውን አስደናቂ ሙከራ ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር በግሩም ቅልጥፍና መልሶበታል።

በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አካላዊ ንክኪዎች ሲቆራረጥ የነበረው ጨዋታ እየተቀዛቀዘ ሄዶ ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ፈታኝ አልነበሩም። ሆኖም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሀዲያ ሆሳዕናዎች 11 የአቻ ውጤቶችን በመያዝ በሪከርዳቸው ሲቀጥሉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በአንጻሩ መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ተጋጣሚያቸው እንደጠበቁት ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ውስጥ እንደነበር እና ለማስከፈት ያደረጉት ጥረትም ፈታኝ እንዳልነበር በመጠቆም በመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ እንደፈለጉት እንዳልተንቀሳቀሱ ሲናገሩ የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው በማጥቃት እንቀስቃሴያቸው ዛሬ ተቀዛቅዞ እንደነበር እና መሃል ሜዳ ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።