ከሀዋሳ ከተማው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ጋር የተደረገ ቆይታ

👉 “አርዓያዬ ለብዙ ክለቦች የተጫወተው ታላቅ ወንድሜ ኢብራሂም ሱሌይማን ነው።” 

👉 “በቡድናችን ውስጥ ያለው ፍቅር ነው እኔንም ጥሩ እንድሠራ ያደረገኝ።”

👉”ሁሌም አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚነግረኝን ነው ለማድረግ የምሞክረው።”

👉 “እዚህ እንድመጣ ላደረገኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ትልቅ ክብር እና ምስጋና አለኝ።”

ኑሯቸውን በሳውዲ አረቢያ አድርገው ለነበሩ ኤርትራዊያን ወላጆቹ አምስተኛ ልጅ ነው። ትውልዱ ሳውዲ ይሁን እንጂ የአንድ ዓመት ልጅ እያለ ቤተሰቦቹ ጠቅልለው ወደ ኤርትራ በመጓዛቸው ዕደገቱ በኤርትራ ሆኗል። ለቀይ ባሕር ፣ ማየት ኮመም ፣ አኽሪያ እና ደንደን የተጫወተውን ታላቅ ወንድሙን ኢብራሂም ሱሌይማን እያየ በእግርኳስ ፍቅር እንደወደቀም ይናገራል። ሆኖም በአስመራ ሊግ ለሚገኘው ቀይ ባሕር ለተባለ ቡድን ከተጫወተ በኋላ በ2013 መገባደጃ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባህር ዳር ከተማ በተደረገው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር ላይ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆኑ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በነበሩት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዐይን ውስጥ በመግባቱ ኢንስትራክተሩ በቀጣዩ ዓመት ፊርማቸውን ለባህር ዳር ከተማ እግርኳስ ክለብ ሲያኖሩ ተጫዋቹን ወደ ቡድናቸው ውስጥ ቀላቅለውታል። በዚህም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው እና በዘንድሮው ውድድር ላይ ለሀዋሳ ከተማ ሰባት ግቦችን በስሙ ከማስመዝገቡ ባሻገር ግሩም እንቅስቃሴ በማድረግ ደምቆ እየታየ ያለው ፈጣኑ አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን!
ሶከር ኢትዮጵያም ከተጫዋቹ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

በእግርኳስ ዕድገትህ አርዓያህ ማን ነበር ?

“ወንድሜ! ኢብራሂም ሱሌይማን ይባላል ፤ ለማየት ኮመም ፣ አኽሪያ እና ደንደን ይጫወት ነበር። እሱን እያየሁ እና እየተከተልኩ ፣ ወደ ጨዋታ ሲሄድ አብሮ ይዞኝ ይሄድ ስለነበር እሱ የደረሰበት ቦታ ለመድረስ ፍላጎቱ ነበረኝ። እግርኳስን መውደድ እና መጫወት እንዳለብኝ እየነገረኝ በእሱ ነው እዚህ የደረስኩት።”

የሀዋሳ ከተማ ቆይታህ እንዴት እየሄደ ነው ?

“ዘንድሮ በሀዋሳ ከተማ ቆይታዬ ትንሽ ለየት ያለ እና ደስ የሚል ነገር ነው። እንደ ቡድን ጥሩ ነገር ስታደርግ ነው ጥሩ ነገር የምትሠራው እና ሀዋሳ በጣም ተመችቶኛል። ያሉት ተጫዋቾች በጣም ጎበዞች ናቸው ከእነሱ ጋር ተግባብቼ አሪፍ ነገር ለመሥራት እና በጥሎ ማለፉ ወይም በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሀሳብ አለን።”

ከጨዋታ በፊት የተጋጣሚ ተጫዋቾችን እንቅስቃሴ የማጥናት ልምድ አለህ?

“አዎ ከጨዋታ በፊት የተጋጣሚ ቡድንን ጨዋታ ማየት እወዳለሁ። እንደ ቡድን እንቅስቃሴያቸውን አይተን ነው የምንሄደው እንደ ግል ደግሞ የተጋጣሚ ተከላካዮች ላይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ከጨዋታ በፊት አይቼ ነው የምሄደው።”


የዘንድሮ እንቅስቃሴህ ጥንካሬ ምንጩ ምንድን ነው ?

“ዋናው ነገር አሰልጣኙ የሚልህን መስማት ነው። እሱ ያለኝን ነገር ለማድረግ ከተጫዋቾቹ ጋር ተነጋግረን ልምምድ ላይ በደንብ ሠርተን መግባባት እንዳለብን አውቀን ተከላካይ ፣ አማካይ እና አጥቂ ሁሉም ቦታ ላይ ያለን ነገር ጥሩ ስለሆነ ሜዳ ላይ አንቸገርም። በተለይ አሁን አሁን ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር ለመሥራት በደንብ ነው እየተግባባን ያለነው። ከጨዋታ በፊት እና በኋላ እናወራለን። ልምምድ ላይ አሰልጣኙ የሰጠንን ነገር በደንብ እንሠራለን ፤  በቡድኑ ውስጥ ያለው ፍቅር ነው እኔንም ጥሩ ነገር እንድሠራ ያደረገኝ ብዬ አስባለሁ።”

የሚዲያ ትኩረት መብዛት የበለጠ ያበረታኛል ብለህ ታስባለህ ወይስ የሚፈጥርብህ ጫና ይኖራል ?

“ዐይን ውስጥ እንዳለሁ አውቄ የበለጠ እንድሠራ ነው የሚያደርገኝ። ብዙ የሚቀረኝ ነገር አለ ፣ ብዙ ነገር ማድረግ ነው የምፈልገው። ከዚህ በላይ የተሻለ ነገር ማድረግ ስለምፈልግ እና ብርታት ስለሚሆነኝ ጠንካራ ለመሆን እና ለቡድኔ ከዚህ የተሻለ ለማገልገል ስለማስብ ያግዘኛል እንጂ የሚፈጥርብኝ ጫና የለም።”

ከቤተሰቦችህ ጋር የተለያየ ሀገር መኖርህን ለመድከው?

“ከመጣሁ ሦስት ዓመት ነው የሆነኝ። ጥሩ ነገር አማርኛ ቋንቋ መልመዴ ነው። እንደመጣሁ ባህር ዳር ላይ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በሚመራው የባህር ዳር ከተማ ቡድን ውስጥ በጥሩ መግባባት ነበር ያሳለፍኩት። ደጋፊዎችም ተጫዋቾችም በደንብ ነበር የተንከባከቡኝ አማርኛ ለመልመድ ብዙ አልተቸገርኩም በዛም እንደ ቤቴ ነው የማስበው እና የቀለለኝ። ሀዋሳ ስመጣ ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ  ጀምሮ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እና ተጫዋቾች ደስ የሚል ባሕርይ ነው ያላቸው። ለዛም ይመስለኛል ብዙ አይከብደኝም ከቤተሰብ ጋር እንዳለሁ ነው የማስበው። የምፈልገውን ነገር ስጠይቃቸው በጣም አሪፍ በሆነ ሁኔታ ያደርጉልኛል። ባህር ዳር እያለሁም ጥሩ ነበር እዚህም ከአብዱልባሲጥ ከማል ጀምሮ ጓደኞቼ ስላሉ ከእነሱ ጋር እየተግባባሁ ባህር ዳርንም ሆነ ሀዋሳን እንደ ቤቴ ነው የማያቸው ፤ ቤቴ እንዳለሁ ነው የማስበው።”

በቦታህ ከሚጫወቱ ሌሎች የሊጉ ተጫዋቾች የተለየ አለኝ የምትለው ነገር አለ?

“ብዙ የተለየ ነገር አለኝ ብዬ አላስብም። እኔ እንደ አጥቂ ሀዋሳ ከእኔ የሚፈልገውን ጎል ከሆነ ጎል አሲስት ከሆነ አሲስት ጥሩ እንቅስቃሴም ከሆነ አሰልጣኝ ዘርዓይ የነገረኝን ነው ሁሌም ለማድረግ የምሞክረው። ሜዳ ስገባ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ፣ እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለብኝ ሁሌም ስለሚነግረኝ ያንን ለማድረግ እና በየጨዋታው የሚሰጠኝን ሚና ለመወጣት ነው የምሞክረው። ልምምድ ላይ የሚሰጠኝን ነገር ሜዳ ላይ ለማድረግ ማለት ነው።”

ከምትፈጥራቸው በርካታ የግብ ዕድሎች አንጻር ያስቆጠርኩት ግብ በቂ ነው ብለህ ታስባለህ ?

“አይደለም! በጣም ብዙ ይቀረኛል። ጎል ላይ እንደምደርሰው ቢሆን እስካሁን 17 ጎል ይኖረኝ ነበር። ጓደኞቼም አሰልጣኞችም የሚሉኝ ነገር ነው። ሳጥን ውስጥ ስደርስ በጣም ስለምቸኩል  መረጋጋት እንዳለብኝ ነው የሚነግሩኝ። ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ደግሞ የተሻለ ነገር እያደረግኩ ፣ ድሬዳዋ ደግሞ ሜዳው በጣም ምቹ ስለሆነ የምቸኩልበት እና የማባክነው ኳስ ይኖራል ብዬ አላስብም። ያለብኝ የአጨራረስ ችግር ላይ ደግሞ አሰልጣኝ ዘርዓይ እያሠራኝ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ ነገር እሠራለሁ ፤ የሚባክኑ ኳሶች ወደ ጎል ይቀየራሉ የሚል ዕምነት አለኝ።”

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ስኬታማ ለመሆን አስፈላጊ ሆኖ ያገኘኸው ነገር ምንድን ነው?

“በመጀመሪያ አስፈላጊው ነገር እንደ ቡድን ጠንካራ ቡድን መሆን አለብህ። ቡድንህ ጠንካራ ከሆነ ጠንካራ ተጫዋች ትሆናለህ እና የበለጠ ያለህን አቅም አስፍተህ ስትሠራ የተሻለ ተጫዋች ትሆናለህ የሚል ዕምነት አለኝ። ከዚህ በኋላ የተሻለ ነገር ለመሥራት ከቡድኔ ጋር ተነጋግረን በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራውን ሀዋሳ ከተማ እና ጠንካራውን ዓሊ ሱሌይማን ማየት እፈልጋለሁ። ካሉ አጥቂዎች ጋርም ተፎካካሪ ለመሆን አስባለሁ።”

ወደ ሊጉ ለሚመጡ ታዳጊዎች ምን ትላቸዋለህ ?

“ሁሌ የሚታይ እና የሚባል ነገር ነው። ባሕር ዳርም  እያለሁ ሀዋሳም ብዙ አቅም ያላቸው ታዳጊዎች አሉ። ያን አቅም በአግባቡ መጠቀም እና ታላላቆቻቸውን ማክበር አለባቸው። የተሻለ ነገር ለመሥራት ደግሞ ዲስፕሊን ዋና አስፈላጊ ነገር ስለሆነ የሚጎድላቸውን ነገር ከታላላቆቻቸው ጋር ተነጋግረው እንደዛ ቢያደርጉ የሚል ዕምነት አለኝ።”

ኳስ ተጫዋች ባትሆን ምን ትሆን ነበር ?

“አብዛኞቹ ጓደኞቼ ቢዝነስ ማን ናቸው ከኳስ ውጪ ቢዝነስ ላይ ጥሩ ነበሩ እና ኳስ ተጫዋች ባልሆን ነጋዴ መሆን እፈልግ ነበር።”

ከኳስ ውጪ በምንድን ነው ጊዜህን የምታሳልፈው ?

“ከኳስ ውጪ በአብዛኛው የማሳልፈው ከልምምድ በኋላ ማረፍ እና መተኛት ነው የምፈልገው ከዛ በኋላ መጻሕፍትን ማንበብ እና የትላልቅ አጥቂዎችን እንቅስቃሴ ዩቲዩብ ላይ እየገባሁ አያለሁ።”

እዚህ ለመድረስህ የምታመሰግናቸው ሰዎች ካሉ…

“መጀመሪያ ሰናፍ ላይ የነበሩ የኔ አሰልጣኞች እነ ኸዋኒ ፣ ሐመድ ጀማል ፣ ወድሃጂ እና አኺሚድ ናቸው እዚህ እንድደርስ ያደረጉኝ ኤርሚያስ ተወልደኪሉ ፣ ዳንኤል ግራኝ እና አለምሰገድ ኤፍሬም የሚባሉ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች የነበሩትንም በጣም አመሠግናለሁ። እዚህ እንድመጣ ላደረገኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ትልቅ ክብር እና ምስጋና አለኝ። እዚህም ላለው አሰልጣኝም ዘርዓይ ሙሉ ጥሩ ነገር እያሠራኝ ስለሆነ በጣም አመሠግናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ለእናንተም ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ በጣም አመሠግናለሁ።