መረጃዎች | 70ኛ የጨዋታ ቀን

18ኛ ሳምንት የሊግ መርሃግብር ነገ ጅማሮውን ያደርጋል እኛም በመጀመሪያ የጨዋታ ዕለት የሚከወኑትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከተ መረጃ በተከታዩ መልኩ አቅርበናል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የጨዋታ ሳምንቱ በተጠባቂ መርሃግብር ጅማሮውን ሲያደርግ በሶስት ነጥብ ልዩነት ብቻ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ባህር ዳር ከተማዎችን አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገናኛል።

በ26 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በሊጉ አናት እየተፎካከሩ የሚገኙት መቻሎች ላይ የተቀዳጁት ድል ከሶስት ነጥብም በላይ ዋጋ የነበረው እንደሆነ ይታመናል ፤ ከዚህ ባለፈ ቡድኑ ከመጨረሻ ሶስት የሊግ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል አድርጎ በአንዱ አቻ የመለያየቱ ጉዳይ ቡድኑ ከደካማ የመጀመሪያ ዙር ጉዞው ማግስት እያገገመ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። ታድያ በመነቃቃት ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ስለመሻሻላቸው ማረጋገጫ ለመስጠት የነገው ጨዋታ ዓይነተኛ ፈተና እንደሚሆናቸው ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬን ወደ ኃላፊነት ካመጡ በኃላ በሊጉም ሆነ በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ለአስራ አንድ ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግዱ የተጓዙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በመጨረሻ ደቂቃ የበረከት አማረ ስህተት ሽንፈትን ለማስተናገድ የተገደዱ ሲሆን ከዚህ መነሻነት በፍጥነት ወደ ቀደመው መንገድ ለመመለስ በነገው ጨዋታ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚያዩት ይጠበቃል።

በ29 ነጥቦች በሰንጠረዡ በ4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች የነገውን ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በሊጉ ፉክክር ውስጥ ስለመቆየታቸው ማረጋገጨ የሚሰጡባቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።

በጣና ሞገዶቹ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ሲታወቅ በቡናማዎቹ በኩል ግን ጫላ ተሺታ ነገም በጉዳት የማይኖር ሲሆን መሐመድኑር ናስር ግን ከጉዳት ተመልሶላቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ9 ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ ሦስት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ አምስቱ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታቸውም ቡድኖቹ እኩል 15 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ሀምበርቾ ከ አዳማ ከተማ

ምሽት 1 ሰዓት ላይ የሚጀምረው መርሃግብር ደግሞ በሊጉ ግርጌ የሚገኙቶን ሀምበርቾዎችን በሰንጠረዡ አጋማሽ ከሚገኙት አዳማ ከተማዎች የሚያገናኝ ይሆናል።

ባልተጠናቀቁ የወረቀት ጉዳዮች ምክንያት በሜዳው ጠርዝ ተገኝተው እስካሁን ቡድኑን መምራት ባይችሉም በልምምድ ሜዳ ሆነ በዝውውር ሂደት ላይ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ሀምበርቾን በሊጉ ለማቆየት ከፍተኛ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።

አሁን ላይ በሰባት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሀምበሪቾዎች ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመላቀቅ አሁን ባለው ሁኔታ የሚጠበቅባቸውን የሰባት ነጥቦች ልዩነት ለማጥበብ ከወዲሁ ሳይረፍድ ነጥቦችን መሰብሰብ ካልቻሉ ፈተናው እየከበደ እንደሚሄድ ይገመታል።

ድል ካደረጉ አራት ጨዋታዎች ያለፋቸው አዳማ ከተማዎች በ24 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ስብስባቸው ከማጠናከር ይልቅ ተጫዋቾችን እየለቀቁ የመገኘታቸው ጉዳይ ለአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ሆነ ለክለቡ ደጋፊዎች ስጋትን ያጫረ ጉዳይ ሆኗል።

አድናን ረሻድን በቅጣት የሚያጡት አዳማ ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ባልተከፈለ ደሞዝ ምክንያት ልምምድ አቁሞ የነበረው አማካዩ ቻርልስ ሪባኑ ዳግም ከቡድኑ ጋር ልምምድ ስለመጀመሩም እንዲሁ ለማወቅ ችለናል።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ባተገናኙበት ጨዋታ 2-2 ተለያይተዋል።