መቻል ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታ አቅርቧል

መቻል እግርኳስ ክለብ የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር አመራር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ላይ ያስተላለፈውን ቅጣት እንደማይቀበል አሳውቋል።

የ2016 ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2ኛ ዙር ውድድር በ17ኛ ሳምንት መቻል ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ወቅት የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኝ ላይ ለጠብ የሚያነሳሳ የሥነምግባር ድርጊት ፈጽመዋል በሚል አራት ጨዋታ እንዲታገዱ እና አምስት ሺህ ብር እንዲከፍሉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ ማሳወቁ ይታወሳል።

ሆኖም የመቻል እግርኳስ ክለብ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጉዳዮች እንደምክንያት ጠቅሶ ማለትም ፦

1) አሰልጣኙ በዕለቱ በነበረው ጨዋታ ከተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኝ ጋር ምንም ዓይነት ለፀብ የሚያነሳሳ ድርጊት ያልፈፀመ በመሆኑ ፊልሙ የሚያሳየው በሰላም ተለያይተው መሄዳቸውን እና ለዚህም ማረጋገጫ ያለን መሆኑ ፣

2) አሰልጣኙ ችግር አለበት ከተባለም ከዚህ በፊት እንደሚደረገው ተጠርቶ ማነጋገር ሲገባቸው ይህ ሳይደረግ አሰልጣኙ በማያውቀው ሁኔታ የተወሰነበት በመሆኑ ፣

3) አሰልጣኙ ፈፀመው ለተባለው ድርጊት የቀረበ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ

የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ መቻል እግርኳስ ክለብ የተሰጠውን የቅጣት ውሳኔ የማይቀበለው መሆኑን በጥብቅ በማሳወቅ ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሔ ይሰጥበት ዘንድ በሚል ጥያቄ ማቅረቡን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ የላከው መረጃ ያመላክታል።