ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ቦሌ ክፍለ ከተማ ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ቅ/ጊዮርጊስ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድሉን ሲያሳካ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

ቀን ስምንት ሰዓት ሲል በጀመረው መርሃግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከልደታ ክ/ከተማ ያገናኘ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨራሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠሩት ግብ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

ልደታ ክፍለ ከተማዎች የጨዋታ ብልጫ መውሰድ በጀመሩት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ በርካታ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

ቅ/ጊዮርጊስ በአንፃሩ ደካማ እንቅሰቃሴ ያደረጉበት አጋማሽ ቢሆንም ግባቸው እንዳይደፈር ወደኋላ አፈግፍገው በመከለካል ሲጫወቱ ተስተውለዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስም ልደታ ክፍለ ከተማ ከተጋጣሚው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መጫወታቸውን ቢቀጥሉም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ግብ ለማግባት በተደጋጋሚ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

የፊት መስመር ተጫዋች ለሆነችዋ ለትመር ጠንክር ታሳቢ ያደረጉ ኳሶች በተደጋጋሚ ቢደርሷትም በደካማ አጨራረስ ኳሶችን መጠቀም ሳትችል ቀርታለች።

ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ የቆዩት ጊዮርጊሶች አከታትለው ባደረጓቸው የተጫዋቾች ቅያሪ የተሻለ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ያለግብ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ በቀሩበት ቅፅበት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ይዘው በመግባት ተቀይራ በገባችው በቃልኪዳን ወንድሙ አማካኝነት ባስቆጠሯት ግብ በስተመጨረሻም የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል አሳክተው ለመውጣት በቅተዋል።

በማስከተል 10 ሰዓት ሲል በጀመረው መርሃግብር ቦሌ ክፍለ ከተማን ከአዳማ ከተማ አገናኝቶ ጨዋታው በነጥብ መጋራት ተፈፅሟል።

ጠንካራ ፉክክር በታየበት የ10 ሰዓቱ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ በቁጥር በርከት ያለ የግብ ሙከራ በሁለቱም ቡድኖች አስመልክቶናል።ቦሌ ክፍለ ከተማዎች መዳረሻቸውን የፊት መስመር ተሰላፊዋን ትዕግሥት ወርቁ ላይ ባደረጉ ኳሶችን ረጃጅም ኳሶች በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል።

አዳማ ከተማ በአንፃሩ በሳባ ኋይለሚካኤል እና በሄለን እሸቱ በተሰለፉበት መስመር በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞከራ ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴን አድርገዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ቦሌዎች ጨዋታው እንደተጀመረ በ47ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኙትን አጋጣሚ ትዕግሥት ወርቁ ከመረብ ጋር አገናኝታ መሪ እንዲሆኑ አድርጋለች።

በዚህ ብቻ ያላበቁት ቦሌዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በጫና ሲጫወቱ ለመመለከት ችለናል ፤ ግብ በማስተናገዳቸው ተስፋ ያልቆረጡት አዳማዎች እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጥር ጥረት ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ በተለይም በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ የጣለው ንፋስ አዘል ዝናብ ለአዳማዎች ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል።መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩት የቦሌ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት ከተገኘውን የቆመ ኳስ አጋጣሚ ሳባ ኃይለሚካኤል አክርራ በመምታት ከመረብ ጋር አገናኝታ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጋለች።