ከፍተኛ ሊግ | ደሴ ከተማ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” የሁለተኛ ዙር 15ኛ የጨዋታ ሳምኝት ሶስተኛ ቀን ውሎ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ደሴ ከተማ እና ባቱ ከተማ በተመሳሳይ ውጤት ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ረፋድ 3 ሰዓት ላይ የጀመረው ቀዳሚው መርሃግብር ደሴ ከተማ ኦሜድላን 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ መጀመሪያ ደቂቃዎች ኦሜድላ ጥሩ በሚባል መልኩ የጀመሩት ነበር ፤ በአንፃሩ በደሴ ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ያለመረጋጋት የተስተዋለበት ነበር።

ደሴ ከተማዎች በጊዜ ሂደት ራሳቸውን በማረጋጋት ወደ ጨዋታ መመለስ የቻሉ ሲሆን በ36ኛው ደቂቃ በግሩም ቅንጅት ተቀባብለው ወደ ኦሜድላ የግብ ክልል በመድረስ አዲስ ግርማ ወደ ግብነት በቀየራት ኳስ መምራት ጀምረዋል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ደሴ ከተማ ይበልጡን ተነቃቅተው ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲፈጥሩ የተስተዋለ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተገባዶ በተጨመሩት ደቂቃዎች ደሴ ከተማዎች ፀጋ ደርብ ለአቡሽ ደርብ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አቡሽ ደርብ ኳሷን በኦሜድላ ግብ ጠባቂ ላዬ ከፍ አድርጎ በማስቆጠር አጋማሹ በደሴ ከተማ የ2-0 በላይነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ አስችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ኦሜድላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የተወሰነ ጥረት ቢያደርጉም በደሴ ከተማዎች በኩል ጨዋታውን በመቆጣጠር እና በተደራጀ የኳስ ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ተመልክተናል።በ68ኛው ደቂቃ ላይ የደሴ ከተማ ተጫዋቹ ሙሉጌታ ካሳሁን በራሱ ጥረት ያስቆጠራት ኳስ የደሴ ከተማን የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል። ጨዋታውም በደሴ ከተማ የ3-0 አሸናፊነት ተገባዷል።

በማስከተል 5 ሰዓት ሲል በጀመረው ጨዋታ ባቱ ከተማ ቦዲቲን 3-0 ማሸነፍ ችሏል።

በመጀመሪያ አጋማሽ ፍፁም የተሻለን ጊዜ ያሳለፉት ባቱ ከተማዎች ሲሆን በአንፃሩ ቦዲቲዎች ደግሞ በመከላከል እና አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃቶ ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። በ14ኛው ደቂቃ የባቱ ከተማ ተጫዋች የሆነው እስራኤል ሸጉሌ አመቻችቶ ያቀበለውን ብርሀኑ አዳሙ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ቦዲቲ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ጠንካራው የባቱ ከተማ ተከላካይ ክፍልን አልፎ ለማስቆጠር ተስኗቸው አጋማሹ በባቱ ከተማ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ባቱ ከተማ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በ76ኛው ደቂቃ በባቱ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ተማም ከድር ላይ በተሠራው ጥፋት ዳዊት ቹቹ የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የቦዲቲ ከተማን አለመረጋጋት የተመለከቱት ባቱ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና በመፍጠር በ83ኛው ደቂቃ አቤኔዘር ዝቋላ ከዮሀንስ ደረጄ ጋር በመቀባበል ከርቀት አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በባቱ ከተማ የ3-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።