የከፍተኛ ሊግ | የ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ስድስት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀመሩ በምድብ ሀ ሞጆ ከተማ ፣ ስልጤ ወራቤ እና ወልዲያ ፣ በምድብ ለ ደግሞ የካ ክፍለ ከተማ ባለ ድል ሆነዋል።


ምድብ ሀ (ሀዋሳ ከተማ)

የሳምንቱ የመጀመሪያ በሆነው ጨዋታ ሞጆ ከተማን ከንብ ያገናኘ ነበር። ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን የቡድኖቹ የመጀመሪያው አርባ አምስት የጨዋታ ጊዜ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን መመልከት ብንችልም ወደ ግብ ደርሶ የተሻሉ ጥቃቶችን በመሰንዘሩ ንቦች የተሻሉ ሆነው ተስተውሏል። በተደጋጋሚ በተለይ በናትናኤል ሠለሞን አማካኝነት ያለቀላቸውን ዕድሎች ቡድኑ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም እንደነበራቸው የሙከራ ብልጫ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ አጋማሹ ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ቀጥሎ ንብ የተጫዋች ለውጥን ጭምር በማድረግ ወደ ሜዳ መመለስ ቢችሉም በአጋማሹ ከፍ ያለ ተነሳሽነትን ያሳዩት ሞጆ ከተማዎች በቀላሉ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል በሽግግር በማለፍ ጎል ማስቆጠር ጀምረዋል። 52ኛው ደቂቃ ከግራ በኩል ግሩም ሽፈራው ያቀበለውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ያገኘውን ያሬድ ሽመልስ ከመረብ አገናኝቷታል። ከሁለት ደቂቃዎች መልስ አዱኛ ገብረመድህን በንብ ተከላካዮች መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ አቤኔዘር ሽመልስ እየገፋ ወደ ሳጥን ገብቶ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል። ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ የቀጠሉት ሞጆዎች 80ኛው ደቂቃ የንቡ ተከላካይ ትኩሱ ጌታቸው በሳጥን ውስጥ ቴዲ ጌታቸው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው እዮብ አለሙ አስቆጥሮት ጨዋታው በሞጆ ከተማ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

እጅግ ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን ከቀትር መልስ የተደረገው ጨዋታ ስልጤ ወራቤን አሸናፊ አድርጓል። ቤንች ማጂ ቡናዎች ጨዋታው ተጀምሮ 2 ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ ከመስመር የተሻገረን ኳስ ሐሰን ሁሴን ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ከአንድ ደቂቃ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ፈአድ መሐመድ ከቀኝ ወደ ውስጥ የላካትን ኳስ ስዩም ደስታ በማስቆጠር ወራቤን አቻ አድርጓል። ወራቤዎች ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት በተደጋጋሚ ጫናን በሚያሳደሩ ፈጣን እንቅስቃሴዎች በመጠቀም ጥቃት መሰንዘር ቢችሉም አጋማሹ 1ለ0 ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

የመሸናነፍ ስሜት ጎልቶ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢስተዋልም የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት በመለወጥ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ደካሞች ነበሩ። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ በቀኝ በኩል ፉአድን በይበልጥ በመጠቀም የማጥቂያ ምንጭ ማድረግ የጀመሩት ስልጤ ወራቤዎች ፉአድ 76ኛው ደቂቃ ከዚህ ቦታ ወደ ውስጥ የላከለትን ኳስ ኪዳነማርያም ተስፋዬ በቀላሉ አግብቶ ስልጤ ወራቤን 2ለ1 አሸንፎ እንዲወጣ አስችሏል።

የመጀመሪያ ቀን የማሳረጊያ በሆነው የኮልፌ ቀራኒዮ እና ወልዲያ ጨዋታ ነበር። እጅግ የተቀዛቀዘ መልክ እና ከሙከራዎችም አኳያ ተዳክሞ ከታየው የመጀመሪያው አርባ አምስት በተወሰነ መልኩ ተሻሽሎ በታየው ሁለተኛው አጋማሽ ወልድያ ከተማዎች በተሻጋሪ እና ረጃጅም ኳሶች መጫወት መጀመራቸው በቀላሉ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ክልል ደርሰው ሙከራዎችን ማድረግ እንዲችሉ ሲያደርጋቸው በአጋማሹ ተመልክተናል። 64ኛው ደቂቃ ቢኒያም ላንቃሞ ከግራ በኩል ወደ ጎል ለማሻማት የላካት ኳስ መረቡ ላይ ተቀምጣ ወልዲያዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ተጨማሪ ጎልን ለማስቆጠር በንቃት መሳተፋቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ ካሊድ መሐመድ ልጆች 70ኛ ደቂቃ አማኑኤል ተስፋዬ ከቅጣት ምት ያሻገራትን ኳስ ተጠቀሞ አለኝታ ማርቆስ ቡድኑን 2ለ0 አድርጓል። ጨዋታው ሊገባደድ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ በብርቱ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የታገሉት ኮልፌዎች 90+5 ላይ ከማዕዘን የተገኘን ኳስ ዋቻሞ ፓውሎስ ከማስተዛዘኚያ ያልዘለለት ግብ በማድረግ ጨዋታው በመጨረሻም በወልድያ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ምድብ ለ (አዲስ አበባ ከተማ)

የምድብ ለ ጨዋታዎችም በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ዛሬ ጅምራቸው አድርገዋል። ረፋድ ላይ ቀዳሚ የነበረው የሸገር ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። በውጤቱም ሸገር ከተማ ነጥቡን ወደ መሪዎቹ ከፍ የሚያደርግበትን ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

8፡00 ሲል በጀመረው የወሎ ኮምቦልቻ እና ካፋ ቡና ጨዋታ 2ለ2 በሆነ የአቻ ውጤት ፍፃሜን አግኝቷል። ከዕረፍት በፊት ካፋ ቡናዎች በመታሰቢያ ገዛኸኝ እና የ5ኛ እና በቢኒያም ካሳሁን የ38ኛ ደቂቃ ጎሎች መሪ መሆን ቢችሉም ከዕረፍት መልስ ወሎ ኮምቦልቻዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ኪሮስ 75ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ ቢላል ገመዳ ከመረብ ያገናኙዋቸው ኳሶች በመጨረሻም ጨዋታው 2ለ2 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች የካ ክፍለ ከተማ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን ያገናኘው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የአሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው የካ 47ኛው ደቂቃ ላይ በደረጀ ነጋሽ ብቸኛ ጎል አሸንፎ ወጥቷል።