የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ጀምረው ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ አዲስ አበባ ከተማ እና መቻል ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ 3:00 በጀመረው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከሀምበርቾ ተገናኝተው በሲዳማ ቡና የበላይነት ተጠናቋል። ሲዳማ ቡና ፍፁም የጨዋታ በላይነት በወሰደው በዚህ ጨዋታ ከዕረፍት በፊት እና ከዕረፍት መልስ ባስቆጠሯቸው ግቦች ማሸነፍ ችለዋል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በረጃጅም ኳሶች ወደ ተቃራኒ ቡድን ሲገቡ የተሰተዋሉት ሲዳማ ቡናዎች የመጀመሪያ ግብ ለማስቆጠር 6 ደቂቃ ብቻ ነበር የጠበቁት። በ6ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ ቅብብል የገቡት ሲዳማ ቡናዎች በፊርማዬ ከበደ አማካኝነት መሪ መሆን ችለዋል። እንዲሁም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በመግባት ለግብ የተቃረቡ በርከት ያሉ ሙከራዎችን አድርገዋል።


ሀምበርቾ በአንፃሩ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በመልሶ ማጥቃት አንዳንድ ሙከራዎችን ቢያደርገም ዒላማውን የጠበቀ አደገኛ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም። እንዲሁም ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን አግኝተው ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ተስተውለዋል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ በሲዳማ ቡና 1ለ0 መሪነት ተጠናቆ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ግለቱን ጨምሮ ሳቢ የሆነበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። ሲዳማ ቡናም ሙሉ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ49ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ማህሌት ምትኩ በራሷ ጥረት ኳስን ይዛ ገብታ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝታ ግብ ጠባቂዋ ወጣ ማለቷን አይታ በቀላሉ ከፍ አድርጋ ኳስና መረብ አገናኝታ የሲዳማ ቡናን መሪነት አጠናክራለች።

ሀምበርቾዎች ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። እንዲሁም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ደካማ እንቅሰቃሴ ያደረጉበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራዎችም ብልጫ ተወስዶባቸዋል።

የሀምበርቾን መዳከም የተረዱት ሲዳማ ቡናዎች ኳስ መስርተው በመጫወት እና ወደፊት በመግባት በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በ65ኛው ደቂቃ ዝናቧ ሽፈራው ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝታ ሲዳማ ቡና 3ለ0 እንዲመራ ሆኗል። ሲዳማ ቡና እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉም ተስተውለዋል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ በሲዳማ ቡና 3ለ0 መሪነት ተገባዶ ጭማሪ በታየው ውስጥ አስቴር ደግአረግ በንክኪ የተገኘውን ኳስ 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ሀምበርቾን ከሽንፈት ያልታደገቻቸውን ግብ አስቆጥራ ጨዋታው 3ለ1 እንዲጠናቀቅ አድርጋለች።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ቀን 10:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከመቻል አገናኝቶ በአቻ ተጠናቋል።

ሳቢ በነበረው በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደግብ ሲደርሱ ለመመለከት ተችሏል። ሆኖም ግን መቻል በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ በማድረግ የተሻለ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ በአንፃሩ በመልሶ መጥቃት የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከደጋፊዎች ጩኸት ጋር የታጀበው ይሄኛው ጨዋታ ሌላኛውን ድምቀት ከደጋፊዎች ዘንድ አግኝቷል።

ጥሩ የጨዋታ ፉክክርም ለተመልካች ባስመለከተው በዚህ ጨዋታ በአንደኛው አጋማሽ ብቻ ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያለ የግብ ሙከራ አድርገዋል። ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ያለምንም ግብ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ጠንከር ብለው የገቡ ሲሆን ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። መቻል ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ነበር። በ60ኛው ደቂቃ ሕይወት ረጉ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝታ መቻሎች መሪ ሆነዋል። ሆኖም ግን ለመሪነት መቆየት የቻሉት ለሁለት ደቂቃዎች ብቻ ነበር።


መቻሎች ግብ አስቆጥረው ደስታቸውን ገልፀው ሳይጨርሱ በሚዘናጉበት ቅፅበት አዲስ አበባዎች ኳስን ይዘው በመግባት በ62ኛው ደቂቃ በቤተልሔም መንተሎ አማካኝነት የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። አቻ ከሆኑ በኋላ ጨዋታው ፉክክሩ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት የግብ ማግባት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።ሆኖም ግን ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ በመጋራት ተገባዷል።