ከፍተኛ ሊግ | ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ መሪነታቸውን አጠናክረዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ16ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የሁለቱም ምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ድራማዊ ክስተቶች በበዙበት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማም ድል ቀንቶታል። ይርጋጨፌ ቡና እና ቢሾፍቱም ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል።

በምድብ ሀ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ወደ መሪዎቹ ከፍ የሚልበትን ዕድል ያመከነበትን ውጤት አስመዝግቧል። 8 ሰዓት ሲል ይርጋጨፌ ቡናን ያስተናገደው የመዲናይቱ ክለብ በመጀመሪያው አጋማሽ አስር ደቂቃዎች ውስጥ የነበራቸውን ብልጫ ተከትሎ 5ኛው ደቂቃ ላይ ቧይ ኩይት ወደ ጎል መትቷት ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ አካሉ የተፋትን ኳስ ምስጋናው ፈግሳ ከመረብ አሳርፏት ቡድኑን መሪ አድርጓል።


ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ በመግባት እንቅስቃሴያቸውን እያሳደጉ የመጡት ይርጋጨፌ ቡናዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ አየነው ሠለሞን በአግባቡ የሰጠውን ኳስ ኃይለአብ በቀለ ቡድኑን ወደ አቻነት ያሸጋገረችን ጎል ለቡድኑ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታው ሊገባደድ አራት ያህል ደቂቃዎች ብቻ በቀሩበት ሰዓት አየነው ሠለሞን በድጋሚ በተከላካይ መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ኃይለአብ በቀለ ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል በማድረግ ሲመራ የነበረውን ቡድን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሚመራው አዲስ አበባ የተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም በፈጣን መልሶ ማጥቃት አጋማሹን ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ይርጋጨፌ ቡናዎች የመዲናይቱን ክለብ የተከላካይ ክፍል ድክመት በመጠቀም 50ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎልን አክለዋል። ከቀኝ የሜዳው ክፍል አቤኔዘር ከፍያለው ያቀበለውን ኳስ ሔኖክ ሞገስ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አድርጓታል። አዲስ አበባ ከተማ የእንቅስቃሴ የበላይነትም በመያዝ ጎልን ለማስቆጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም ደካማ ከነበረው የመከላከል አደራደር አኳያ 90+5 ላይ አማኑኤል ከበደ አራተኛ ጎል አስቆጥሮባቸው ጨዋታው በይርጋጨፌ ቡና 4ለ1 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመቀጠል ድራማዊ ክስተቶች በተበራከቱበት የመሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ ጎል ኤሌክትሪክ ወሳኝ ሦስት ነጥብን አግኝቷል። ከእንቅስቃሴዎች ውጪ በሙከራዎች እምብዛም ያልደመቀው የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ሜዳ ላይ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ያስመልክቱን እንጂ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተለይ በአቤል ሀብታሙ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉበት እና የጅማ አባጅፋሩ አንጋፋ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ ያለቀላቸውን ኳሶች ከጎልነት በተደጋጋሚ የታደገበትን ሂደት አስተውለናል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተሻለ ፉክክርን ከበርካታ ያልተገቡ ድርጊቶች ጋር መመልከት የቻልንበት ሁለተኛው አጋማሽ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ የተመለሱት እና ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር ከክፍያ ጉዳይ ጋር የተለያዩት አባ ጅፋሮች መሪ የሆኑበትን ጎል ከመረብ አሳርፈዋል። 56ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሔኖክ ገብረሕይወት ያሻማትን ኳስ ከተከላካይ ጀርባ ሆኖ ያገኘው ማንያዘዋል ካሳ በቀላሉ አስቆጥሯታል። ወደ አቻነት ለመመለስ በብርቱ ጥረት ያደረጉት ኤሌክትሪኮች በቢኒያም ካሳሁን ፣ አንዋር በድሩ እና ቢኒያም ካሳሁን አማካኝነት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝረው አልቀመስ ብሎ የዋለው ዮሐንስ በዛብህ የተደረጉትን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከጎልነት ሲታደጋቸው ተመልክተናል።

ጨዋታው ቀጥሎ 72ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ያሬድ የማነ ከማዕዘን ያሻማለትን ኳስ አቤል ሀብታሙ በግንባር ገጭቶ መረቡ ላይ በማሳረፍ ኤሌክትሪክን 1ለ1 ማድረግ ችሏል። ሊጠናቀቅ በተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ ድራማዊ የሆኑ በርካታ ክስተቶችን ጨዋታው አስመልክቶናል። የዕለቱ ዋና ዳኛ ሶሬሳ ካሚል ስድስት ደቂቃዎችን በጨመሩበት ወቅት የኤሌክትሪኩ አጥቂ አቤል ሀብታሙ ኳስን እየገፋ ወደ ሳጥን ሲገባ በተከላካዮች መጠለፉን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ አሚር አብዶ የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ዳኛውን በመደብደቡ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተጫዋቹ ከመወገዱ በተጨማሪ ተጠባባቂው ግብ ጠባቂ አማን ከድር ከአራተኛ ዳኛው ጋር በፈጠረው ግርግርም በቀይ ካርድ ከተወገደ በኋላ ጅማዎች በዳኛው ላይ ክስን አስይዘው ረዘም ላሉ ደቂቃዎች የተቋረጠው ጨዋታ ከተመለሰ በኋላ 90+10 ላይ ቢኒያም ካሳሁን ፍፁም ቅጣት ምቷን ከመረብ አዋህዶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተመሪነት ወደ መሪነት መጥቷል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅትም ጅማ አባጅፋሮች በሔኖክ ገብረሕይወት አማካኝነት የአቻነት ጎልን ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ኳሷ መባሏን ተከትሎ ከረዳት ዳኛው ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የገባው የጅማ አባጅፋር ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሮባ ወርቁ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ ጨዋታው በስተመጨረሻ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የምድብ ለ ሁለት ጨዋታዎችም በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ሲከናወን መሪው አርባምንጭ ውጤቱን ሲያጠናክር ቢሾፍቱ ከተማም አሸንፏል። ረፋድ 5 ሰዓት ላይ የምድቡ መሪ አርባምንጭ ከተማ ተጋጣሚው ደብረብርሃን ከተማን በመርታት ጣፋጭ ድልን አስመዝግቧል። ከዕረፍት መልስ 77ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው አህመድ ሁሴን ያስቆጠራት ግብ አዞዎቹን አሸናፊ ያደረገች ብቸኛ ጎል ሆናለች።

በመቀጠል በአሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመራውን ቢሾፍቱ ከተማን ከ ኦሜድላ ያገናኘው ጨዋታ 1ለ0 በሆነ ውጤት የቢሾፍቱ የበላይነት ተፈፅሟል። 58ኛው ደቂቃ ላይ አብዱላዚዝ ዑመር ብቸኛዋን ጎል ከመረብ ያሳረፈው ተጫዋች ሆኗል።