አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ራሳቸውን ከኃላፊነት አነሱ

አሠልጣኝ ተመስገን ዳና ከሀምበርቾ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል።

ከሳምንታት በፊት በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና እና በሀምበርቾ ክለብ መካከል በተደረገ የውስጥ ስምምነት መሠረት 17ኛ እና 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በልምምድ ቦታ ሲያዘጋጁ ቢቆዩም ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር በተያያዘ የወረቀት ሥራዎች ባለማለቃቸው ቴክኒካል ቦታ ላይ ሳይሆኑ ቡድኑን በኃላፊነት ተረክበው ሲሠሩ ቆይተዋል።

አሁን እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከዚህ በኋላ ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ለክለቡ ማስገባታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ በላኩት መረጃ አሳውቀዋል። እንደ አሰልጣኙ ገለፃ ከሆነ ራሳቸውን ከኃላፊነት ለማንሳት የተገደዱበትን ምክንያት ሲያብራሩ “ከቀድሞ አሰልጣኝ የውል ጉዳይ ጋር ተያይዞ መሰናክሎች የበዛበት ነው። ይህ ደግሞ በልምምድ ሜዳዎች እና በጨዋታ ወቅት ሥራዬን በነፃነት እንዳልሰራ አድርጎኛል። በዚህም የመጣሁበትን ዓላማ ማሳካት ስለማልችል በፍጥነት ነገሮች እንዲስተካከሉ ከቀናት በፊት በደብዳቤ ባሳውቅም በክለቡ በኩል ምንም ምላሽ ያላገኘሁ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ከክለቡ ጋር መቀጠል ለክለቡም ለግል ሥራዬም ጥሩ ስለማይሆን የጀመርኩትን ሥራዬን ማቋረጤን አሳውቃለሁ።” በማለት ገልፀዋል።

ሀምበርቾ ከ18 ጨዋታዎች አንድ አሸንፎ አራት አቻ በመውጣት በአስራ ሦስት ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዶ ሰባት ነጥብ በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል።