ሪፖርት | ዋልያዎቹ አዞዎቹን ረተዋል

ዛሬ በተደረገው ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ሌሶቶን 2ለ1 ማሸነፍ ችላለች።

9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ዋልያዎቹ በተሻለ ግለት ጨዋታውን መጀመር ችለው 9ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስቆጥሩ እጅግ ተቃርበው ነበር። ቸርነት ጉግሳ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሆኖም ሌሶቶዎቹ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ሲጫወቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደራጅቶ ለመግባት ሲቸገር ተስተውሏል።

ጨዋታው 32ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዞዎቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሌህሎሆኖሎ ፎቶአኔ ከቀኝ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ የግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን መዘናጋት ተጨምሮበት የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ግብ ሆኗል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተጭነው መጫወት የቻሉት ዋልያዎቹ 38ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው አብነት ደምሴ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በተከላካይ ተጨርፎ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያዊያን 42ኛው ደቂቃ ላይም በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ወሳኝ የግብ ዕድል ፈጥረው መስፍን ታፈሰ አብዱልከሪም ወርቁ ባመቻቸለት ኳስ በቀኝ መስመር ከሳጥን ውጪ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገው ሙከራ አጥሮበት ግብ ጠባቂው ሞሬኔ ሴኮሃኔ አቋርጦበታል።

ከዕረፍት መልስ አቤል ያለውን በመስፍን ታፈሰ ቢኒያም ዐይተንን ደግሞ በአብዱልከሪም ወርቁ ቀይረው ያስገቡት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ውጤታማ ሆነዋል። በዚህም 51ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ያገኘው ቸርነት ጉግሳ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በሚያገኟቸው ኳሶች ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት ዋልያዎቹ 61ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። ያሬድ ካሳዬ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሞሬኔ ሴኮሃኔ ሲመልስበት ኳሱን ያገኘው ከነዓን ማርክነህ በቀላሉ ግብ አድርጎታል።

ሌሶቶዎች የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት እየተቸገሩ ቀጥለው 86ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። ሽመክት ጉግሳ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው ተገልብጦ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የላይ አግዳሚ መልሶበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታውም በኢትዮጵያ የ2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።