የበጋው ዝውውር መስኮት ሲጠቃለል

ከቀናት በፊት በተዘጋው የውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት የተጠናቀቁ ዝውውሮች ምን መልክ ነበራቸው?

የዝውውር መስኮቱ ከቀናት በፊት ተዘግቷል። ክለቦች ሻምፒዮን ለመሆን፣ ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ ወይም የአፍሪካ መድረክ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ቦታ ይዘው ለማጠናቀቅ ያግዙናል ያሏቸው ዝውውሮች አጠናቀዋል። የዝውውር መስኮት ገበያው እንደ ከዚ ቀደሙ የደራ አልነበረም። በክለቦች ያጋጠመው የገንዘብ እጥረት በገበያው አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድርም በለስ ቀንቷቸው ተጫዋቾች ያስፈረሙ ክለቦች ግን ጥቂት አይደሉም። ነገሮች በየእለቱ በፍጥነት በሚለዋወጡበት ሁኔታ የቡድኖቹን እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታተል በርካታ ዜናዎች ወደ እናንተ በማቅረብ ላይ የቆየችው ሶከር ኢትዮጵያ በተገባደደው መስኮት የተካሄዱት ዝውውሮች በጥቅሉ ለማየት የሞከረችበት ፅሑፍ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

ኢትዮጵያ መድን

ከውድድር ዓመቱ መጀመር አስቀድሞ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው አጥተው ውድድራቸውን የጀመሩት መድኖች አስደንጋጩ የመጀመርያ ዙር ውጤት ለመቀየር በርካታ ተጫዋቾች አስፈርመዋል። በተጠናቀቀው የዝውውር መስኮት እሸቱ ከበደ ወደ ዋናው ቡድን አሳድገው ጄሮም ኦዴ ፍሊፕ፣ አቡበከር ሳኒ፣ አብዲሳ ጀማል፣ አለን ካይዋ፣ ሀይደር ሸረፋ፣ ሚልዮን ሰለሞን፣ ተክለማርያም ሻንቆና አናንያ ጌታቸው ያስፈረመው ክለቡ ስምንት ተጫዋቾች በማስፈረም ቀዳሚ ነው።

ሻሸመኔ ከተማ

በአመዛኙ በወራጅ ቀጠናው የከረሙት ሻሸመኔ ከተማዎች አራት ተጫዋቾች በማስፈረም የዝውውር መስኮቱን አገባደዋል። የግብ ማስቆጠር ችግራቸውን ለመፍታት የፊት መስመር ተጫዋቾች ለማስፈረም የመረጠው ቡድኑ ከወልቂጤ ከተማና ኢትዮጵያ ቡና በስምምነት የተለያዩት ስንታየሁ መንግስቱና ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ እንዲሁም ብሩንዳዊ አጥቂ አልፍሬድ ንኩሩንዚዛ ስያስፈርም
የኢትዮጵያ ቡናው ገዛኸኝ ደሳለኝ ውሰት ውል ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ሀምበርቾ

ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣትና የለቀቁባቸው ተጫዋቾች ለመተካት እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ የተንቀሳቀሱት ሀምበሪቾዎች አምስት ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል። በሦስቱም የሜዳ ክፍሎች ያላቸውን ክፍተት ለመሙላት ዝውውሮች የፈፀመው ክለቡ አማካዮቹ ብርሀኑ አሻሞና በሀይሉ ተሻገር፤ ተከላካዮቹ ሙና በቀለና አዲስዓለም ተስፋዬ ስያስፈርሙ ለአስራ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻለውን የፊት መስመር ለማሻሻል ደግማ ካሪም ንድጉዋ የተባለ ዩጋንዳዊ አጥቂ አስፈርሟል።

ባህርዳር ከተማ

ሁለት መልክ ያለው የውድድር ዓመት በማሳለፍ ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ያጋጠማቸው የውጤት ውጣ ውረድ ለመፍታት የሚያስችሉ ሦስት ዝውውሮች ፈፅመዋል። ቡድኑ ፀጋዬ አበራ፣ ወንድወሰን በለጠና ከሀዋሳ ከተማ ጋር በስምምነት የተለያየው ሙጂብ ቃሲም አስፈርሟል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቀደም ብለው አጥቂያቸው አቤል ያለው ለግብፁ ክለብ አሳልፈው የሰጡት ፈረሰኞቹ ወሳኙ አጥቂያቸው ለመተካት ትልቅ ዝውውር ይፈፅማሉ ተብሎ ቢጠበቅም ክፍተቱን በተስፈኛ ወጣቶች ለመሙላት መርጠዋል። ቡድኑ በአርሲ ነገሌ ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ያሳየው ታምራት ኢያሱና አማካዩ ክንድዓለም ፍቃዱን ከሸገር ሲቲ አስፈርሟል።

መቻል

ከባለፉት ዓመታት በተለየ ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን የገነቡት መቻሎች በጥራትና በጥልቀት የተሻለውን ስብስባቸው ለማጠናከር ቁልፍ ዝውውር አጠናቀዋል። ቀደም ብለው እንደተፈለገው ውጤታማ ካልሆነው ናይጀርያዊ አጥቂ ቺጂኦኬ አኩኔቶ ጋር በስምምነት የተለያየው ጦሩ ተጫዋቹን ለመተካት ቀናት አልፈጀበትም። ቡድኑ የቶጎ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ የሆነው አብዱ ሞታላብ በማስፈረም ቡድኑን አጠናክሯል።

ሲዳማ ቡና

ከአደጋው ቀጠና ለመራቅ አልመው ውድድራቸውን በማካሄድ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ሁለት ተጫዋቾች በማስፈረም ስብስባቸውን አጠናክረዋል። ከዚ ቀደም በአርባምንጭ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና መጫወት የቻለው ኢማኑኤል ላርዬና በንፋስ ስልክ ላፍቶ አስራ ሦስት ግቦች በማስቆጠር ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ያሳየው አጥቂው ሄኖክ ፍቅሬ ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ሀድያ ሆሳዕና

ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን ገንብተው እንደሚፈለገው ፍሬአማ መሆን ያልቻለ የፊት መስመር ያላቸው ሀድያ ሆሳዕናዎች የፊት መስመራቸው የውጤታማነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ
የቀድሞ ተጫዋቻቸውን ማስፈረም መርጠዋል። ላለፉት ስድስት ወራት በኢራቁ ናፍት አል ዋሳት ቆይታ የነበረው ባለ ልምዱ ዑመድ ኡክሪ የነብሮቹ የፊት መስመር የማሻሻል ኃላፊነት ለመረከብ ቡድኑን ተቀላቅሏል።

ፋሲል ከነማ

ከመሪው በሰባት ነጥቦች ርቀው የተቀመጡት ዐፄዎቹ ስብስባቸውን ለማጠናከር የሁለት ተጫዋቾች ዝውውር አገባደዋል። ጠንካራ የተከላካይ ክፍል የገነቡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ክፍሉ ይበልጥ ለማጎልበት ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ ስያስፈርሙ በደደቢት መለያ ሊጉን የተዋወቀውና ላለፉት ስድስት ወራት በሀምበሪቾ ቆይታ ያደረገው አፍቅሮተ ሰለሞን አስፈርመዋል።

ድሬዳዋ ከተማ

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል መገንባት የቻሉት ብርቱካናማዎቹ ፊታቸውን ወደ ማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በማዞር አንድ የፊት መስመር ተጫዋቾች በማስፈረም ክፍተታቸውን ለመሙላት ጥረት አድርገዋል። ከወልቂጤ ከተማ ጋር በስምምነት የተለያየው አሜ መሐመድም በተደጋጋሚ ጉዳትና ቅጣት ምክንያት የሳሳውን የብርቱካናማዎቹ የፊት መስመር ለማጠናከር የፈረመ ብቸኛ ተጫዋች ነው።

ኢትዮጵያ ቡና

በሂደት ወደ ሊጉ አናት የሚያስጠጋቸውን ውጤት አስመዝግበው ከመሪው በስምንት ነጥቦች ርቀው የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ታዳጊዎች ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ ካደረጉት ጥረት በተጨማሪ የአንድ ተጫዋች ዝውውር አጠናቀዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት በኤሌክትሪክ ማልያ ሲጫወት የከረመው አማካዩ ስንታየሁ ዋለጬ ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ሊጉ የሚመልሰው ዝውውር በመፈፀም በመስኮቱ ቡናማዎቹን የተቀላቀለ ብቸኛ ተጫዋች ሆኗል።

ሀዋሳ ከተማ

በጊዜ ሂደት በሊጉ አስፈሪ የፊት መስመር ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆኑት ሀይቆቹ አንድ ተጫዋች በማስፈረም የፊት መስመር አማራጫቸው አስፍተዋል። ወደ እናት ክለቡ ዳግም የተመለሰው
ግዙፉ እስራኤል እሸቱም ለቋሚነት የሚደረገው ብርቱ ፉክክር አሸንፎ በቂ የመጫወቻ ጊዜ የሚያገኝ ከሆነ ለቡድኑ ለየት ያለ አማራጭ ይሰጣል ተብሎ ይታመናል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከዓመታት በኋላ በተመለሱበት ሊግ ሳይጠበቁ ከወዲሁ ለዋንጫ ከሚታጩ ቡድኖች አንዱ የሆነው ቡድን የገነቡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ፈርጣማው ስብስባቸው ለማጠናከር የአንድ ተጫዋች ዝውውር አጠናቀዋል። በርካታ የፊት መስመር አማራጮች ያሏቸው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የተከላካይ መስመራቸውን ማጠናከርን መርጠዋል። ቡድኑን የተቀላቀለው ደግሞ ከዚ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች በአሰልጣኙ ስር የሰራውና ያለፉትን ስድስት ወራት በሻሸመኔ ከተማ ቆይታ የነበረው ሁለገቡ ተመስገን ተስፋዬ ነው።

የቅርብ ዓመታት ታሪክ እንደሚያሳዩት ክለቦቻችን በክረምቱም ሆነ በበጋው የዝውውር መስኮት ተጫዋችች ለማስፈረም ንቁ ነበሩ። በተጠናቀቀው የጥር የዝውውር መስኮት ግን ምንም እንኳ አብዛኞቹ ማለትም አስራ ሦስት ክለቦች ቡድናቸውን ለማጠናከር ዝውውሮች ቢፈፅሙም ገበያው እንደከዚ ቀደም በርካታ ውሎች የተፈፀሙበት አልነበረም።