ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ወልዲያ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ድል አድርገዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 18ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሦስት መርሃግብር ተከናውነው ወልዲያ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ድል ሲያደርጉ የንብ እና የስልጤ ወራቤ ጨዋታ ተቋርጧል

የረፋድ ሦስት ሰዓቱ ጨዋታ ጅማ አባ ቡናን ከወልዲያ አገናኝቶ ወልዲያ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠሩት ግብ አሸንፈዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ወደግብ ከመሄድ ይልቅ ወደኋላ አፈግፍገው በጥንቃቄ ሲጫወቱ ተስተውለዋል። እምብዛም የግብ ሙከራ ባይታይም ወልዲያ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ። ቢሆንም ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል።ጅማ አባ ቡና በአንፃሩ በረጃጅም ኳሶች ግብ እንዳይቆጠርባቸው ከግብ ክልል ሲያፀዱ ተስተውለዋል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቆ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስም በመጀመሪያው አጋማሽ የታየው አይነት ጨዋታ ያስመለከቱ ሲሆን ወልዲያ ከአንደኛው አጋማሽ አንፃር ተሽለው የገቡበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። በዚህም ኳስ መስርተው በመጫወት ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። መድረሻቸውን ቢንያም ላንቃሞ ላይ ባደረጉ ኳሶች ግብ ለማግባት ጥረት ያደረጉት ወልዲያዎች የፊት መሰመር አጥቂያቸው ኳሶችን ሲያመክን ለመመለከት ተችሏል። እንዲሁም ረጁም የፊት መሰመር ተጫዋች በድሩ ኑሩሀሴን ኳሶችን ሳይጠቀም ሲቀር ተስተውሏል። ጅማ አባ ቡናም በአንፃሩ አንዳንዴ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ቢጥረም የጨዋታ ብልጫ ሙሉ ለሙሉ ለወልዲያ ያስረከቡበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ለጠናቀቅ 3 ደቂቃ ሲቀረው በድሩ ኑሩሀሴን በራሱ ጥረት ኳስን እየገፋ ወደግብ ክልል በመጠጋት ግብ ጠባቂው መውጣቱን አይቶ በቀላሉ ከፍ በማድረግ ኳስና መረብ አገናኝቶ ወልዲያን አሸናፍ አድርጎ ጨዋታው ተጠናቋል።

በማስከተል የሰዓት ለውጥ ተደርጎበት 5:00 ላይ ኦሮሚያ ፖሊስ ከጅማ አባ ጅፋር ያገናኘው መርሃ ግብር በኦሮሚያ ፖሊስ በላይነት ተጠናቋል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ የግብ ሙከራዎች መታየት በጀመሩት በዚህ ጨዋታ ኦሮሚያ ፖሊስ በኳስ ቁጥጥር እያ በግብ ሙከራ የተሻሉ ነበሩ። ጅማ አባ ጅፋር በአንፃሩ ግብ እስኪያስተናግድ  በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል። በ9ኛው ደቂቃ ሁለት ቁጥር ለባሹ ሰለሞን አለሙ  ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ ጋር ተገናኝታ ኦሮሚያ ፖሊሲን መሪ እንዲሆን አስችላለች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ጅማ አባ ጅፋሮች ተረጋግተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ለመመለከት ተችሏል። ሆኖም ግን ጠንካራ ሆኖ የዋለውን የኦሮሚያ ፖሊስ ተከላካይ መሰመር አልፎ ግብ ማስቆጠር ተሰኗቸው ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ኦሮሚያ ፖሊስ ጠንከር ብሎ በመግባት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና አሳድርዋል። በ64ኛው ደቂቃ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኃይሌ ዘመድኩን በንክኪ የገኘችዋን ኳስ በማግኘት ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ለኦሮሚያ ፖሊስ መሪነቱን አስፍቷል። ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ኦሮሚያ ፖሊሶች በአንድ ለአንድ ቅብብል በመግባት ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሚችሉበትን አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ተስተውለዋል። ጅማ አባ ጅፋሮች ግን ደካማ የኳስ ቁጥጥር እና የግብ ሙከራ ያደረጉበትን ሁለተኛ አጋማሽ ለማሳለፍ ተገደዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ላይ በተደጋጋሚ ግብ መሆን ሚችሉበተን አጋጣሚ ሳይጠቀም ሲቀር የነበረው ድንኤል ዳርጌ በግሩም አጨራረስ ሦስተኛ ግብ ለኦሮሚያ ፖሊስ አስቆጥሮ ጨዋታው በኦሮሚያ ፖሊስ 3ለ0 በሆነ ውጤት ተገባዷል።

የሳምንቱ ማሳረጊያ የነበረው የእለቱ ሦሰተኛ ጨዋታ በስልጤ ወራቤ እና በንብ መካከል ተደርጓል። በጨዋታው ጅማሮ የንቡ ታምራት ሥላሴ 7ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ግብ ቡድኑን ቀዳሚ ቢያደርግም 31ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ደስታ ስልጤ ወራቤን አቻ ማድረግ ችሏል። ሆኖም ከዕረፍት በፊት በሀዋሳ ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጨዋታው 1ለ1 በሆነ ውጤት በ63ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጧል።