ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጎል ፌሽታ ሀምበርቾን ረምርሟል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዕረፍት መልስ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሀምበርቾን 5-1 በመርታት የሊጉን አናት ተቆናጧል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ወቅት ከተጠቀሙት አሰላለፋቸው በአራት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን ሲያደርጉ በረከት ግዛው ፣ ፉአድ ፈረጃ ፣ ኪቲካ ጀማ እና ቢኒያም ጌታቸው አርፈው በምትካቸው ተስፋዬ ታምራት ፣ ብሩክ እንዳለ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና ሲሞን ፒተር ወደ ሜዳ ሲገቡ  ሀምበርቾዎች ከሀድያ ሆሳዕናው ሽንፈታቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ፓሉማ ፓጆምን በምንታምር መለሠ ፣ ዲንክ ኪያርን በታሪኩ ታደለ እንዲሁም በረከት ወንድሙን በአብዱልከሪም ዱጉዋ ተክተዋል።

በዝናባማ የአየር ፀባይ ውስጥ ሆኖ ወደ ሊጉ ዘንድሮ ያደጉትን ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ከወትሮው ከፍ ባለ ተነሳሽነት ወደ መስመር ባጋደሉ ሽግግሮች የሚጫወቱት ሀምበርቾዎች በኳስ ቁጥጥሩ በተጋጣሚያቸው ይበለጡ እንጂ ጎልን ለማስቆጠር በእጅጉ የተቃረቡባቸውን አጋጣሚዎች ሲፈጥሩ ተመልክተናል። 14ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የንግድ ባንክ ሳጥን ውስጥ የደረሰውን ኳስ አዲሱ ጋናዊ የሀምበሪቾ አጥቂ አብዱልከሪም ንዱጉዋ ከግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ጋር ተገናኝቶ ፍሬው በጥሩ ብልጠት ኳሱን ከግብነት አግዶበታል። በረጅሙ ወደ መስመር በሚጣሉ እና ወደ ሳጥን በፍጥነት ኳስን በማድረስ በመከላከሉ ረገድ ወረድ ብለው የቀረቡትን የንግድ ባንክ ተከላካዮችን ሲፈትኑ የነበሩት የተራራ አናብስቶቹ ተሳክቶላቸው  23ኛው ደቂቃ ላይ የመሪነት ግባቸውን አግኝተዋል።

ከማዕዘን ምት ምናሴ ብራቱ ያሻገረውን ኳስ አላዛር አድማሱ የአምና ክለቡ ላይ ኳሷን በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ እየገቡ የመጡት ንግድ ባንኮች ኳስን በመቆጣጠር በአንድ ሁለት ቅብብል አልያም ደግሞ ከአማካይ ክፍላቸው ከሚነሱ ተለጣጭ እና የመስመር ተጫዋቾቻቸውን ባማከሉ ኳሶች ወደ አቻነት ለመምጣት መትጋት ጀምረዋል።

ፈቱዲን ጀማል ከራሱ የሜዳ ክፍል በረጅሙ ያሻገራትን ኳስ ኤፍሬም ታምራት በግንባር ገጭቶ ምንታምር መለሠ በቀላሉ የተቆጣጠረበት የቡድኑ ቀዳሚ ሙከራ ስትሆን በተለይ ደግሞ 31ኛው ደቂቃ በቅብብል በጥሩ የእግር ስራ ብሩክ እንዳለ በተከላካዮች መሐል ለተገኘው ባሲሩ ዑመር ያሾለከለትን ኳስ አማካዩ ከግብ ጠባቂው ምንታምር ጋር ቢገናኝም ወጣቱ የግብ ዘብ በጥሩ ብልሀት ኳሷን አስጥሎታል።

40ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት በገጠመው ብሩክ እንዳለ ምትክ ፉአድ ፈረጃ የተኩት ንግድ ባንኮች ከቆሙ ኳሶች በሽግግር የጨዋታ መንገድ አቻ በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል ለማምራት ቢታትሩም የቡድኑ የፊት ተሰላፊዎች ስል አለመሆን በመጀመሪያዎቹ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ጥሩ የግብ ዕድሎችን ፈጥረው በነበሩት ሀምበርቾዎች ጨዋታው በ1ለ0 መሪነት ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ተከላካዩ ተስፋዬ ታምራትን በአጥቂው ኪቲካ ጀማ በመተካት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቁጥር ከፍ በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ በብርቱ ጥረት አድርገዋል። ሀምበርቾዎች አጋማሹ በተጀመረ አራት ደቂቃዎች ውስጥ ተቀይሮ የገባው ምንያምር ጴጥሮስ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ አቤል ዘውዱ አግኝቶ ፍሬው ከተቆጣጠረበት በኋላ የንግድ ባንክ የግብ ክልል ለመድረስ አይናፋር እየሆኑ የመጡት ሀምበርቾዎች በተጋጣሚያቸው ሙሉ በሙሉ ለመበለጥ የተገደዱ ሲሆን የኋላ ክፍላቸው በሚሰራቸው ተደጋጋሚ ስህተቶች ጎሎችን ለማስተናገድ ተገደዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ባሲሩ ዑመር በግራ በኩል ኳስን ይዞ ሲገባ አቤል ዘውዱ ሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ በማስቆጠር ጨዋታውን ወደ አቻነት አሸጋግሯል።

ፉአድ እና ባሲሩ መሐል ላይ በንክኪ በሁለቱ ኮሪደር በኩል አዲስ እና ኪቲካን ባማከለ መልኩ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ከመሪነት ወደ ተመሪነት የመጡበትን ግብ አሁንም ከቆመ ኳስ አግኝተዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይ ፉአድ ከቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ የተገኘን የቅጣት ምት ወደ ውስጥ ሲያሻማ ካሌብ አማንኩዋ በግንባር ገጭቶ መረቡ ላይ ኳሷን አሳርፏታል። የንግድ ባንክን ጫና መቋቋም የከበዳቸው እና በሚሰሯቸው ስህተቶች ይበልጡኑ ተጋላጭነታቸው ከፍ እያለ የመጣው ሀምበሪቾዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ ምናሴ በራቱ በሳጥን ውስጥ በኪቲካ ጀማ ላይ ጥፋት በመስራቱ የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አድርጓታል።

ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ባሲሩ ዑመር ወደ ቀኝ ለኪቲካ ሰጥቶት አጥቂው መሬት ለመሬት ወደ ግብ ክልል የላካትን ኳስ ሳይመን ፒተር በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጧታል። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ኪቲካ ጀማ 40 ደቂቃዎችን ሜዳ ላይ ካሳለፈ በኋላ ጉዳት በማስተናገዱ በብሩክ ብፁአምላክ ተቀይሮ ለመውጣት የተገደደ ሲሆን 87ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስም ተቀይረው በገቡ ሁለት ተጫዋቾች ንክኪ ንግድ ባንኮች አምስተኛ ግብን አክተዋል።

ብሩክ ብፁአምላክ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ዳዊት ዮሐንስ ከመረብ አዋህዷል ፣ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው አራት ጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ ሱለይማን ሀሚድ ካመከናት ግልፅ አጋጣሚ በኋላ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊትም ንግድ ባንክ የሊጉን መሪነት ተረክቧል።