መረጃዎች | 83ኛ የጨዋታ ቀን

የ21ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ሀምበርቾ

በዕለቱ የመጀመርያ መርሀ ግብር ተከታታይ ባስመዘገቧቸው ውጤቶች በደረጃ ሰንጠርዡ ዝቅ ያሉት ፋሲል ከነማዎች ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በመጨረሻ ጨዋታቸው በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ዐፄዎቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ቀድመው መሪ ቢሆኑም አስጠብቀው መውጣት አልቻሉም። ቡድኑ ድል ባላስመዘገበባቸው ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ አምስት ግቦች ማስተናገዱ ሲታይም የቀደመ ጠንካራ ጎኑን ያጣ ይመስላል። ከሳምንታት በፊት ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ክለቦች ተርታ የነበረው ፋሲል በቅርቡ የተሻለ የማጥቃት እሳቤን ተላብሶ ቢታይም የተከላካይ መስመር ጥንካሬቅን ማጣቱ ቁጥሮችም ይመሰክራሉ። የዐፄዎቹ የፊት መስመር በነገው ዕለት በቅርብ ሳምንታት በርካታ ግቦች ያስተናገደ ቡድን እንደመግጠሙ በጨዋታው ጠንካራ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ባይታመንም በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ላሉበት ወሳኝ ጨዋታዎች የግብ ክልሉን ያለማስደፈር ብቃቱ መልሶ ማግኘት በእጅጉ ያስፈልገዋል።

በ12ኛው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 2-0 በመርታት የተሻለ መነቃቃት ውስጥ የተጠበቁት ሀምበርቾዎች ከዚያ በኋላ ባደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ግን በአንዱ አቻ ወጥተው በተቀሩት ተረተዋል። ይባስ ብሎም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ያስተናገዷቸው 13 ግቦች በውድድሩ ዓመቱ የተቆጠሩባቸውን ግቦች መጠን 35 አድርሰውታል። ይህም ቡድኑ ትልቅ የአደረጃጀት ክፍተት እንዳለበት ይጠቁማል። በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሀምበርቾዎች ያላቸውን ተስፋ ለማለምለም ከተከታታይ ሽንፈት ወጥተው ከቀሩት መርሀ ግብሮች ነጥብ ማግኘት ግድ ይላቸዋል። ሆኖም ቡድኑ ካለበት የተሸናፊነት መንፈስ ለመውጣት የነገውን ድል በእጅጉ ከሚፈልገው ፋሲል ከነማ የሚጠብቀው ፉክክር ቀላል አይሆንም።

የቡድን ዜናን በተመለከተ በፋሲል ከነማ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል እና አፍቅሮት ሰለሞን በጉዳት ጋቶች ፓኖም በቅጣት ምክንያት እንደማይኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን የአምሳሉ ጥላሁን እና ዓለምብርሃን ይግዛው መሰለፍ አጠራጣሪ ሆኗል። በአንጻሩ ጌታነህ ከበደ ነገ በሙሉ ጤንነት ወደ ሜዳ ይመለሳል። ሀምበርቾዎች ትእግስቱ አበራ ከጉዳት መልስ ማግኘት ቢችሉም ጉዳት ላይ ያለው ምናሴ ቢራቱ ግን በጨዋታው አይሳተፍም።

ፋሲል ከነማ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን ጨዋታ 3-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ባህርዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሳምንቱ ትልቁ መርሀ ግብር ነገ ምሽት የጣና ሞገዶቹን ከፈረሰኞቹ ያገናኛል።

በሁሉም ረገድ ተሻሽለው በውጤታማ ጉዞ ላይ የሚገኙት ባህርዳር ከተማዎች በተከታታይ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች የደረጃ መሻሻል አስገኝቶላቸዋል። የጣና ሞገዶቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ ከኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ ተለያይተው ከጣሉት ነጥብ ውጭ በተቀሩት ጨዋታዋች ድል አድርገዋል። ከዚህ በዘለለም ድሎቹ ጠንካራ ከሚባሉ ቡድኖች ጋር በተደረጉ ጨዋታዎች የተገኙ መሆናቸው ትልቅ ዋጋ አላቸው።
በጥር የዝውውር መስኮት በዋነኝነት የፊት መስመራቸውን የሚያጠናክሩ ዝውውሮች ያከናወኑት የጣና ሞገዶቹ የግብ ማስቆጠር ችግራቸው በዘላቂነት የሚፈታ የፊት መስመር ጥምረት ገንብተው በርከት ያሉ ግቦች ማስቆጠር አልቻሉም። ቡድኑ ተከታታይ ድሎች ካስመዘገበባቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአንዱ ብቻ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠሩም የፊት መስመሩ ተጨማሪ ማሻሻያ እንደሚፈልግ ጠቋሚ ነው።

ሆኖም ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ላይ የሚገኘው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በቀላሉ እንደማይደፈር በተጠባቂ ጨዋታዎችም ጭምር አስመስክሯል። የተከላካይ ክፍል ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል ፤ በተጨማሪም በተጠቀሱት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ነው ያስተናገደው። የመከላከል አደረጃጀቱም የቡድኑ ዋነኛ የጠንካራ ጎን ነው። በነገው ዕለትም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከተቀዛቀዘው የፈረሰኞቹ የፊት መስመር የሚያደርጉት ፍልምያ ጨዋታው ተጠባቂ ያደርገዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታታይ ድሎች መልስ በሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ለመጣል ተገዷል። ይህ መሆኑ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ በጥቂቱ ሸርተት እንዲል እና ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት እንዲሰፋ ያደረግው ሲሆን ተጨማሪ ነጥቦችን መጣል አይኖርበትም። ፈረሰኞቹ በአዳማ ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው በወሳኙ የመቻል ጨዋታ ነጥብ ይዘው መውጣታቸው እንደ አንድ በጎ ጎን የሚታይ ቢሆንም ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ከሀገራት ውድድር መልስ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ተቸግሯል። በነገው ወሳኝ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣትም በዋንጫ ፉክክሩ ከሚኖረው ጠቀሜታ በተጨማሪ ወደ ቀደመ የአሸናፊነት ሥነ ልቦናው ስለሚመልስ ለቡድኑ ያለው ትርጉም ትልቅ ነው።

ከመጨረሻዎቹ ሁለት መርሀ ግብሮች በፊት በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው የጊዮርጊስ የፊት መስመር በቅርብ ጨዋታዎች የማጥቃት ሂደቱ ተፈትኗል። በነገው ዕለትም ጥንካሬ የተላበሰውና ባለፉት አምስት መርሀ ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደውን የጣና ሞገዶቹ የኋላ መስመር የሚፈትን ብቃት ላይ መገኘት ይኖርበታል።
ከዚህ በተጨማሪ ከመቻል ጋር በነበረው ጨዋታ በውስን መልኩ ተጋላጭ የነበረው የኋላ መስመር ማስተካከያዎችን ይሻል። በተለይም ለተጋጣሚ ረዣዥም ኳሶች ምቹ የነበረው ከተከላካዮች ጀርባ የነበረው ሰፊ ክፍት በሚገባ መሸፈን ይጠበቅባቸዋል።

ባህርዳር ከተማዎች ከጉዳትና ቅጣት ነፃ የሆነው ስብስብ ይዘው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግን አማካዩ በረከት ወልዴ በቅጣት አያሰልፉም። በአንፃሩ አማኑኤል ኤርቦ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ለቡድኑ መልካም ዜና ነው።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ሦስት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሁለት ድሎችን አሳክተው አራት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጠኝ ባህር ዳር ከተማ ስምንት ግቦችን አስቆጥረዋል።