ሪፖርት | የምሽቱ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተቋጭቷል

ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተለያይተዋል።

ወላይታ ድቻ ከወልቂጤ ከተማው ሽንፈት ጉዳት የገጠመው መልካሙ ቦጋለን በአዛሪያስ አቤል ፣ የቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት ናትናኤል ናሴሮን በፍፁም ግርማ እንዲሁም ፀጋዬ ብርሀኑን በዘላለም አባቴ በመተካት የዛሬውን ጨዋታ ጀምሯል። ፋሲል ከነማን በመርታት ለዛሬ በደረሰው ድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ ካርሎስ ዳምጠው በኤልያስ አህመድ ቦታ የተተካበት ብቸኛ ለውጥ ተደርጓል።

በጨዋታው ቀዳሚ 20 ደቂቃዎች በተሻለ ተነሳሽነት የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች ተሽለው ታይተዋል። የተጋጣሚያቸውን ኳስ ቁጥጥር በማቋረጥ እና እስከ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በሚደረስ የማጥቃት ጫና በመታጀብ በእንቅስቃሴ እና ከተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶች ዕድሎችን ፈጥረዋል። ከዚህ ውስጥ 6ኛው ደቂቃ ላይ አብነት ደምሴ ከባዬ ገዛኸኝ የተቀበለውን ኳስ በሳጥኑ መግቢያ ላይ ተገኝቶ ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት ይጠቀሳል። አዛሪያስ አቤል እና አበባየሁ አጂሶም ከማዕዘን ምት በተነሱ ኳሶች ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር።

በጨዋታው 20ኛ ደቂቃ አናጋው ባደግ ከያሬድ ታደሰ ጋር ተጋጭቶ በጥርሱ ላይ የደረሰበት አደጋ በእዮብ ተስፋዬ ተለውጦ እንዲወጣ ያስገደደ ሆኗል። ከዚህ አጋጣሚ በኋላ የጦና ንቦቹ ግለት እየበረደ ሲሄድ በአንፃሩ ብርቱካናማዎቹ ከሜዳቸው መውጣት የጀመሩባቸው የጨዋታ ሂደቶች መታየት ጀምረዋል። ሆኖም ቡድኑ ቢኒያም ገነቱን የሚፈትን የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ነበር አጋማሹን የጨረሰው።

ይልቁኑም የቀደመ ብልጫቸውን በጥቂቱ የመለሱት ወላይታ ድቻዎች 34ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ጥቃት ሰንዝረው ሳጥን ውስጥ ቢገኙም ብስራት በቀለ በድሬ ተከላካዮች መሀል ዕድሉን ወደ ሙከራ ሳይቀይር ወድቋል። በሂደቱ ዳግማዊ አባይ ጥፋት ሰርቶበታል የሚለው የቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄም በዕለቱ ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። 44ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከተከላካይ ጀርባ በተጣለ ኳስ የአጋማሹን አደገኛ ዕድል አግኝቶ ሙከራው ለጥቂት በቋሚው ስር የወጣበት አጋጣሚም ወላይታ ድቻ ለግብ የቀረበበት ነበር።

ድሬዳዋ ከተማዎች ስታዲየሙን በሚመጥን ድባብ ለታደመው ደጋፊያቸው አስደስች ቅፅበት ያገኙት በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ነበር። ኬኔዲ ከበደ ከዕረፍት መልስ በዘራዓይ ገብረሥላሴ ተቀይሮ የገባው ሙኸዲን ሙሳ የተላከለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ቀድሞ የነካው ካርሎስ ዳምጠው ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ራሱ ካርሎስ 54ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ከግቡ በኋላም ድሬዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ተጋጣሚያቸውን ወደ ሜዳው ገፍተው መንቀሳቀስ ችለዋል። ሆኖም የመጀመሪያ አጋማሽ ብልጫቸው የተወሰደባቸው ድቻዎች ከኳስ ውጪ ለመቆየት ቢገደዱም አቻ የሚያረጋቸውን ድንገተኛ ቅፅበት ከአስር ደቂቃዎች በኋላ አግኝተዋል። ከሜዳቸው በረጀሙ ከተጣለ እና አበባየሁ አጂሶ ካሾለከው ኳስ ጋር ብዙአየሁ ሰይፉ በሦስት የድሬ ተከላካዮች መሀል አፈትልኮ በመውጣት ከአብዩ ካሳዬ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

_

ከአቻነቱ በኋላ ጨዋታው ጥሩ የማጥቃት ምልልስ እየታየበት ቀጥሏል። ብርቱካናማዎቹ በቅብብሎች ወደ ሳጥን በማድረስ እና ተሻጋሪ ኳሶችን በመላክ የድቻን የተከላካይ ክፍል ሲፈትኑ በመልሱ የጦና ንቦቹ ፈጣን ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል። በተለይም 78ኛው ደቂቃ ላይ ብስራት በቀለ እዮብ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በግንባር ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት ይጠቀሳል።

የአሸናፊነት ጎል ፍለጋ ቡድኖቹ በፉክክራቸው እስከፍፃሜው ቢቀጥሉም በጭማሪ ደቂቃ ቻርለስ ሙሴጌ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሌላ ግብ ጠባቂዎችን መፈተን ሳይችሉ ቀርተዋል። ይልቁኑም ሰከንዶች ሲቀሩ በተጨዋቾች መሀል የተጠረው ጉሽሚያ ትኩረት ስቦ በአበባየሁ አጂሶ እና ሲያም ሱልጣን የቢጫ ካርድ ከተቋጨ በኋላ የምሽቱ ፍልሚያ በ1-1 ውጤት ተፈፅሟል።

አሰልጣኞች በሰጡት ሀሳብ ጨዋታው በጠበቁት ልክ እንዳልነበር የተናገሩት የድሬዳዋው አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ ተጋጣሚያቸው ኳስ እንዳይቆጣጠሩ እንደተጫናቸው ገልፀው ቡድናቸው በወጥነት እየትንቀሳቀሰ እንደሆነ እና የራሱን መልክ እየያዘ ስለመሆኑ ጠቁመዋል። ጠንካራ ፉክክር እንደተደረገ የጉለፁት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው የተጨዋቾች ቅጣት እና ጉዳት እንደማያሳስባቸው ከቅጣት የሚመለሱ ተጫዋቾች እንደሚኖሩ ሲጠቁሙ ለተጫዋቾቻቸው የሰጡትን ታክቲካዊ ዕቅድ ከብዙአየሁ የማጥቃት ባህሪ ጋር አጣምረው አስረድተዋል።