ሪፖርት | ንግድ ባንክ ለአምስተኛ ጊዜ ከመመራት ተነስቶ አሸንፏል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመመራት ተነስቶ ሀዋሳ ከተማን 2ለ1 በመርታት መሪነቱን አጠናክሯል።

በ21ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማ ተገናኝተው ንግድ ባንኮች በ20ኛው ሳምንት ሀምበርቾን 5ለ1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ፉዓድ ፈረጃ እና ኪቲካ ጅማ በተስፋዬ ታምራት እና ብሩክ እንዳለ ተተክተው ገብተዋል። ኃይቆቹ በአንጻሩ በኢትዮጵያ ቡና 3ለ2 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው በረከት ሳሙኤል ፣ አማኑኤል ጎበና ፣ እስራኤል እሸቱ ፣ ማይክል ኦቱሉ እና ሲሳይ ጋቾ በመድሃኔ ብርሃኔ ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ኢዮብ ዓለማየሁ ተተክተው ገብተዋል።

10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 7ኛው ደቂቃ ላይ በፉዓድ ፈረጃ 16ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በሳይመን ፒተር ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ 19ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን ሀሚድ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ባሲሩ ኦማር ያደረገውን ሙከራ በረከት ሳሙኤል በጥሩ ቅልጥፍና አግዶበታል።

መሃል ሜዳው ላይ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዋሳዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርቦ ሱሌይማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሳይመን ፒተር ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሲያባክነው 39ኛው ደቂቃ ላይ ኃይቆቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።  አቤኔዘር ዮሐንስ ከፉዓድ ፈረጃ ተጭኖ የቀማውን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ተከላካዩን ካሌብ አማንክዋህን በድንቅ ክህሎት በማታለል ኳሱን ከግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ከፍ አድርጎ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ፈታኝ መሆን ያልቻሉት ባንኮች 43ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ሙከራ አድርገው ሀብታሙ ሸዋለም ከሳጥን አጠገብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ሲመልስበት 45+3ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ባሲሩ ኦማር ወደ ግብ የላከው ኳስ በእንየው ካሳሁን ተጨርፎ ግብ ሊሆን ሲል ግብ ጠባቂው ጽዮን መልሶታል። የተመለሰውን ኳስ ሳይዘጋጅ ያገኘው ባሲሩም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ከዕረፍት መልስ ግሩም አጀማመር ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 50ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ፉዓድ ፈረጃ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ሳያርቀው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ሳይመን ፒተር በቀላሉ አስቆጥሮታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ራሱ ሳይመን ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ከኤፍሬም ታምራት ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው ጽዮን አድኖበታል።

የማጥቃት ኃይላቸውን በማጠናከር ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 59ኛው ደቂቃ ላይ በካሌብ አማንክዋህ 61ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በባሲሩ ኦማር ሙከራ ካደረጉ በኋላ 65ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ፉዓድ ፈረጃ በጥሩ ሁኔታ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ኪቲካ ጅማ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን ከመመራት ወደ መምራት እንዲሸጋገር አስችሎታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ሀዋሳ ከተማዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለማንሠራራት በመሞከር በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ቢደርሱም 88ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ዓለማየሁ ከሳጥን አጠገብ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ቢመስልም 90+7ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት አውሽ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ድንቅ ሙከራ እና 90+8ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዓሊ ሱሌይማን ከግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ በተሻገረለት ኳስ ያደረጓቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በድንቅ ብቃት መልሷቸዋል። ጨዋታውም ውጤቱ ሳይቀየር በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከዕረፍት በፊት ታክቲካሊ ጥሩ የነበሩ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ በዛ አለመቀጠላቸውን ጠቅሰው በቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ እንዳልነበሩ በመግለጽ በዋና ዳኛው ውሳኔዎችም ደስተኛ እንዳልነበሩ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው አጀማመራቸው ጥሩ እንደነበር ነገር ግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ጠንካራ እንዳልነበሩ በሠሩት ስህተትም ጎል ማስተናገዳቸውን ጠቅሰው ሁለተኛ ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ተጋጣሚያቸው ተጭኖ እንዲጫወት እንደፈቀዱ ገልጸዋል።