መረጃዎች | 82ኛ የጨዋታ ቀን

21ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለት የነገ መርሃግብሮች ዙርያ ተከታዮቹን መረጃዎች አጠናቅረናል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር በሰንጠረዡ አናት የሚገኙትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችን በሰንጠረዡ ወገብ አካባቢ ከሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ያገናኛል።

ከተከታታይ ሳምንታት ውጤት አልባ ጉዞዎች በኃላ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሀምበሪቾ ላይ የግብ ናዳ በማዝነብ ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አሁን ላይ በ40 ነጥቦች ከተከታያቸው መቻል በግብ ክፍያ ልቀው ሊጉን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

በጨዋታው ከድሉ ባሻገር ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አንድ ብቻ ግብ ያስቆጠረው ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ አምስት ግቦችን ከአራት የተለያዩ አስቆጣሪዎች የማግኘቱ ጉዳይ ለአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ሌላኛው አስደሳች ዜና ነው።

የሊጉ የዋንጫ ፉክክር ከሳምንት ሳምንት ጡዘቱ እየከረረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ፉክክር ውስጥ በተፎካካሪነት ለመዝለቅ ከሰሞኑ ከነበሩበት ወጣ ገባ ካለ እንቅስቃሴ ለመውጣት ተከታታይ ድላቸው ለማስመዝገብ የነገው ጨዋታ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት በመጨረሻ ሰከንዶች በኢትዮጵያ ቡና በተቆጠረባቸው ግብ ሽንፈትን አስተናግደው ወደዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የሚመጡት ሀዋሳ ከተማዎች አሁን ላይ በ26 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ከቀደሙት አመታት በተሻለ በአስደናቂ ብቃቅ ላይ በሚገኘው ኤርትራዊው አጥቂያቸው ዓሊ ሱሌይማን የግል ጥረት ታግዘው በርከት ያሉ ግቦችን እያስቆጠሩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች በአንፃሩ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ በመከላከሉ ረገድ በቀላሉ ግብ የሚያስተግዱም ሆነው እያስተዋልን እንገኛለን።

ከነገውም ጨዋታ ቡድኑ ውጤት ይዞ ለመውጣት በማጥቃቱ ከዓሊ ሱሌይማን እንዲሁም በመከላከሉ ከቡድኑ የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት የግድ ይላቸዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መጠነኛ ጉዳት የገጠመው ኪተካ ጅማ ወደ ልምምድ ቢመለስም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን አማካዩ በረከት ግዛው ግን ከቅጣት መልስ ቡድኑን የሚያገለግል ይሆናል በአንፃሩ በሀዋሳ ከተማ በኩል አማካዩ አብዱልበሲጥ ከማል በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል።

በሊጉ በሰላሳ ስድስት ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በአስራ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ንግድ ባንክ በአስራ ሶስት እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በአስር ጨዋታዎች ድል ማድረግ ችለዋል።በጨዋታዎቹ ንግድ ባንኮች ሰላሳ ስምንት እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ሰላሳ ስድስት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋ ከተማ

የምሽቱ መርሃግብር ደካማ ሰሞነኛ ብቃት ላይ የሚገኙትን ወላይታ ድቻዎች መነቃቃት ላይ ከሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ያገናኛል።

በውድድር ዘመኑ ጅማሮ ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴን ከውጤት ጋር አጅበው ሲያስመለክቱን የቆዩት ወላይታ ድቻዎች ሰሞነኛ አካሄዳቸው ግን እጅግ አስደንጋጭ ይመስላል ፤ ካደረጓቸው የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ሽንፈት ሲያስተናግዱ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተው በድንገት ራሳቸውን በ24 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ለማግኘት ተገደዋል።

ከውጤት ማጣታቸው ባለፈ በተከታታይ ጨዋታዎች የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾች አንተነህ ጉግሳ እና ቢኒያም ፍቅሬን በቀይ ካርድ ምክንያት ያጣው ቡድኑ በመጨረሻ ጨዋታቸውም ደግሞ ዘንድሮ ለቡድኑ ቁልፍ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኘውን ወጣቱን ተከላካይ ናትናኤል ናሴሮን በሁለት ቢጫ አጥተዋል።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኃላ በአንፃራዊነት የተነቃቃ ጉዞን እያደረጉ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ከሰሞኑ ከገጠሟቸው ተጋጣሚዎች ጥንካሬ አንፃር እያስመዘገቡ የሚገኙት ውጤት ጥሩ የሚባል ነው አሁን ላይም ቡድኑ በ29 ነጥቦች በ9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በዚህም መነሻነት ቡድኑ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በሚያደርጋቸው ሰሞነኛ ጨዋታዎች የቡድኑ ደጋፊዎች እጅግ በከፍተኛ ቁጥር በሜዳ በመገኘት ለቡድናቸው እየሰጡ ያለው ድጋፍ እጅግ የተለየ ሆኖ እየተመለከትን እንገኛለን ፤ ነገ ምሽትም ቡድናቸው ውጤታማ ሆኖ እንዲወጣ ደጋፊዎች የሚጫወቱት ሚና የላቀ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል በባለፈው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልነበረው ቻርለስ ሙሴጌ ከጉዳት መልስ ወደ ልምምድ ቢመለስም ነገ የመሰለፉ ነገር ሲያጠራጥር ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ያሉት ተመስገን ደረስ፣ ያሲን ጀማል እና አብዱልፈታህ ዓሊ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ አስራ አምስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አምስቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲደመደሙ ድሬዳዋ ከተማዎች በሰባት እንዲሁም ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በሶስቱ ባለድል መሆን ችለዋል በጨዋታዎቹ ድሬዎች አስራ አምስት እንዲሁም ድቻዎች ደግሞ አስራ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።