የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎችን አስተናግዶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጠናክሮ አርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማም ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው የመጀመሪያውን ዙር አገባደዋል።

ረፋድ ሦስት ሰዓት ላይ የተደረገው መርሃግብር ድሬዳዋ ከተማን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገናኝቶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፏል።

ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጨዋታ በላይነት ወስደው ግብ ለማስቆጠር ጫና አሳድረዋል። ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ ግብ እንዳይቆጠርበት ጥረት ያደረገ ሲሆን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያሳዩ አልተስተዋሉም። በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የነበሩት ንግድ ባንኮች ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ የመጀመሪያ ግብ በአርያት ኦዶንግ አማካኝነት በ20ኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል። ሰናይት ቦገለ ጨርሳ የሰጠችውን ኳስ አርያት ኦዶንጎ አግኝታ የመጀመሪያ ግብ አስቆጥራ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መሪ ሲታደርግ ድሬዳዋ ከተማዎች መረጋጋት ተስኗቸው ስህተት ሲሰሩ ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠር አስራ ሦስት ደቂቃ የጠበቁት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ33ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ በእርስ በርስ ቅብብል የተገኘውን ግብ አስገኝታ መሪነታቸውን አስፍታለች። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት በ45ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ቁምነገር ካሳ አግኝታ ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ብታደርግም የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ 2-1 በሆነ ውጤት ዕረፍት ለመውጣት ተገደዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ንግድ ባንክ ጠንከር ብሎ ገብቶ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ከተከላካይ መስመር ጀምሮ ኳስ መስርተው ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ለመግባት ጥረት አድርገው በርከት ያለ የግብ ማግባት ሙከራ እንዲሁም አስቆጪ የሚባሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በዚህም በጫና የሚመጡትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ኳሶችን ከማጨናገፍ ውጪ ግብ ለማስቆጠር ወደፊት ሲሄዱ ብዙም አልተስተዋሉም። በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ንግድ ባንኮች በ72ኛው ደቂቃ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥረዋል። 72ኛ ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ጨርሳ ያቃበለችውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ መረብ ላይ አሳርፋለች። እንዲሁም ብዙም ሳይቆዩ ተጨመሪ ግብ ያስቆጠሩ ሲሆን ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው አርያት ኦዶንግ በራሷ ጥረት ኳስ እየገፋች ይዛ ገብታ አራተኛ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው 4-1 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲያሸንፍ ሆኗል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ መቻልን ከአርባምንጭ ከተማ አገናኝቶ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ብቸኛ ግብ አርባምንጭ ከተማን አሸናፊ አድርጓል።

ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከማራኪ እግር ኳስ አጨዋወት ጋር ያስመለከተው ይሄኛው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እና አልሸነፍ ባይነት የታየበት ጨዋታ ነበር። መቻልም ሆነ አርባምንጭ ከተማ ግብ ለማስቆጠር በርከት ያለ የግብ ሙከራ ያደረጉበት የመጀመሪያ አጋማሽ ለመመለከት ተችሏል። ሆኖም ግን የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም አርባምንጭ ከተማ ጨዋታውን መምራት ችሏል። በ17ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ያገኘችው ፎዚያ መሐመድ በግሩም ሁኔታ አጨራረሷን አሳምራ አርባምንጭ ከተማን መሪ አድርጋለች። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ አርባምንጭ ከተማዎች ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ መቻሎች በተቃራኒው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በማጥቃት ረገድ ብልጫ የወሰዱ ቢሆንም ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ቅያሪ አድርገው ግብ ለማስቆጠር ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በርከት ያለ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ መቻሎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መጫወት ችለዋል። አርባምንጭ ከተማም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመልሶ ማጥቃት የግብ ሙከራ ቢያደርግም ሌላ ተጨማሪ ግብ ማሳየት ግን ሁለቱም ቡድኖች አልቻሉም። 78ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጭ ከተማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ይርጋሸዋ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥታ ጨዋታው ቀሪውን 12 ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል። ይሄንን አጋጣሚ በመጠቀም መቻሎች ግብ ለማስቆጠር ጫና ቢያሳድሩም የአርባምንጭ ከተማን አደራደር አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ለመጠናቀቅ ተገዷል። በዚህም አርባምንጭ ከተማ በፎዚያ መሐመድ ብቸኛ ግብ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

የመጀመሪያ ዙር ማሳረጊያ የሆነው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ ቡና አገናኝቶ በሀዋሳ ከተማ በላይነት ተጠናቋል።

በርከት ካለ ከሀዋሳ ተመልካቾች ጋር የታጀበው ይሄኛው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን አሸናፊ ሲያደርግ በመጀመሪያው አጋማሽ ጠንከራ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ደካማ እንቅስቃሴ ያደረገውን የሲዳማ ቡናን ክፍተት በመጠቀም በተጋጋሚ የግብ ሙከራ በማድረግ ግብ በማስቆጠረም ቀዳሚ የሆኑበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። ሲዳማ ቡናም ሀዋሳ ከተማም  ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጠንከር ያለ እና አደገኛ ሙከራ በማድረግ ረገድ ሀዋሳ ከተማ ብልጫ ወስዷል በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ግብ አስቆጥሯል። በ18ኛው ደቂቃ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ረድኤት አስረሳኸኝ በግሩም አጨራረስ ከመረብ ጋር አገናኝታ ሀዋሳ ከተማን መሪ አድርጋለች። ምንም እንኳን ግብ ቢቆጠርባቸውም ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ጥሩ በመሆን የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ጥሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፈውን የሀዋሳ ከተማን ተከለካይ መስመር አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው እየተመሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ጠንከር ብሎ የገባ ቢሆንም ሲዳማ ቡናም ጥሩ እንቅሰቃሴ ያስመለከት ቡድን ነበር። በግብ ማግባት ሙከራ ጥሩ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ56ኛው ደቂቃ በፊት መስመር አጥቂያቸው አማካኝነት ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል። ከመሰመር አከባቢ የተሻማውን ኳስ ረድኤት አስረሳኸኝ እንዴትም ብላ በመድረስ በግንባሯ ገጭታ ሀዋሳ ከተማ መሪነቱን እንዲያሰፋ አድርጋለች። ሁለተኛ ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ሀዋሳ ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ በመከላከል ስራቸው ተጠምደዋል። ሲዳማ ቡና በተቃራኒ በጫና ግብ ለማስቆጠር ወደፊት ሲሄዱ የተሰተዋሉ ቢሆንም ግብ ሳያስቆጥሩ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ከሽንፈት ያልተደገቻቸውን ግብ  በረቂቅ አሰፋ አማካኝነነት አስቆጥረው ጨዋተው 2-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።