ሪፖርት | ሸምሰዲን መሐመድ ዐፄዎቹን ከሽንፈት ታድጓል

ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የፋሲል ከነማ እና የሀምበርቾ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ሀምበርቾ ተገናኝተው ፋሲሎች በ20ኛው ሳምንት በድሬዳዋ 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አምሳሉ ጥላሁን ፣ ጃቢር ሙሉ ፣ ይሁን እንዳሻው እና ጌታነህ ከበደ በኢዮብ ማቲያስ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ኤልያስ ማሞ እና ፍቃዱ ዓለሙ ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ተካተዋል። ሀምበርቾዎችም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5ለ1 ከተሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ፖሉማ ፖጁ ፣ ትዕግሥቱ አበራ ፣ በኃይሉ ተሻገር እና አብዱልሰላም የሱፍ በምንታምር መለሰ ፣ ምናሴ በራቱ ፣ ታሪኩ ታደለ እና በፍቃዱ አስረሳኸኝ ተተክተው ገብተዋል።

10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ባሕሩ ተካ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበሩት የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ሀምበርቾዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አብዱልሰላም የሱፍ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻማው ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን የግብ ዕድል ፈጥረው ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ያሻገረውን ኳስ ቶሎሳ ንጉሤ በግሩም ቦታ አያያዝ በግንባሩ በመግጨት አስወጥቶባቸዋል።

ከውሃ ዕረፍት መልስ በተለይም በቀኙ መስመር የማጥቃት ኃይላቸውን ያጠናከሩት ዐፄዎቹ በዮናታን ፍስሃ አማካኝነት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ በዚሁ እንቅስቃሴያቸውም 28ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ዮናታን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ አክርሮ በመምታት ግብ ጠባቂው ባጠበበው የግቡ የግራ ክፍል በኩል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

30ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂያቸውን አብዱልከሪም ንዱግዋን በጉዳት አጥተው በረከት ወንድሙን ቀይረው ለማስገባት የተገደዱት ሀምበርቾዎች ጨዋታውን ለማረጋጋት ጥረት አድርገው 45+1ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲሉ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግንባር ገጭቶ ካደረገው ሙከራ ውጪ የተለየ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ሀምበርቾዎች 51ኛው ደቂቃ ላይ ከሳማኬ ሚኬል ለሁለተኛ ጊዜ በተበረከተላቸው ኳስ ግብ አግኝተዋል። ጥሩ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው የግራ መስመር ተከላካዩ አብዱልሰላም የሱፍ  ከግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ተጭኖ የቀማውን ኳስ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ፋሲል ከነማዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው መነሻ የሆነውን ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በጉዳት ምክንያት ካጡ በኋላ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደራጅተው ለመድረስ እጅግ ሲቸገሩ 77ኛው ደቂቃ ላይም ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጨማሪ ራስ ምታት የሚሆን አጋጣሚ ተፈጥሯል። ሀምበርቾዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የወሰዱትን ኳስ በረከት ወንድሙ ሊጠቀምበት ሲል ሀቢብ መሐመድ ከሳጥን አጠገብ ጎትቶ በመጣሉ ዳኛው በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል።

ይበልጥ እየተጋጋሉ የሄዱት የአሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ ተጫዋቾች ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ሲችሉ በተለይም 81ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው በፍቃዱ አስረሳኸኝ በግራ መስመር በግሩም ሁኔታ በመውሰድ ለበረከት ወንድሙ አመቻችቶለት በረከትም በግቡ የግራ ቋሚ ዒላማውን ሳይጠብቅ በወጣ ሙከራ አባክኖታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በርካታ ቅያሪዎችን በማድረግ ተጭነው የተጫወቱት ዐፄዎቹ 86ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለሙ አማካኝነት ከቅጣት ምት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለው በግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ ቢያዝባቸውም 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ በውድድር ዓመቱ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ሜዳ የገባው ሸምሰዲን መሐመድ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ በሊጉ ከታዩ ድንቅ ግቦች መካከል አንዷ የሆነችውን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

ያለባቸውን የድል ረሃብ ለማስታገስ በመቃረባቸው በጉጉት ውስጥ ሆነው የግብ ዕድሎችን ሲያባክኑ የነበሩት ሀምበርቾዎች ድሉን ከእጃቸው ቢያጡትም 90+8ኛው ደቂቃ ላይ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ለማግኘት እጅግ ተቃርበው ቶሎሳ ንጉሤ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው በፍቃዱ አስረሳኸኝ ኳሱን ዓየር ላይ እንዳለ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታውም 2ለ2 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው አሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ ጨዋታው ጥሩ እንደነበር እና ከጨዋታው በፊት ያሰቡትን ነገር ሜዳ ላይ እንዳደረጉ በመግለጽ ከእንቅስቃሴያቸው አንጻር ሁለት ነጥብ ማጣታቸውን ጠቁመው ከዚህ የተሻሉ ሆነው እንደሚቀርቡ ያላቸውን ሀሳብ ሰጥተዋል። የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ቀድመው ጎል ማስተናገዳቸው ጥድፊያ ውስጥ እንዲገቡ እንዳስገደዳቸው በመናገር “ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር” ብለው ከጠቆሙ በኋላ የግብ ጠባቂዎች ስህተት አሳሳቢ እንደሆነባቸው እና ሊታረም እንደሚገባውም በመግለጽ ውጤታቸው ደጋፊውን እንደማይመጥን ሀሳባቸውን ሲሰጡ ዳኞችም ተጫዋቾች ለሚያስተናግዱት ጉዳት በቂ ግብረመልስ እየሰጡ አይደሉም ሲሉም ኮንነዋል።