ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ እና ፈረሰኞቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአማኑኤል ኤርቦ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከባህር ዳር ጋር 1ለ1 ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል።

በሊጉ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች  ሻሸመኔ ከተማን ባሸነፉበት ወቅት ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ፍፁም ጥላሁንን በሙጂብ ቃሲም በብቸኝነት ሲተኩ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከመቻል ጋር ያለ ጎል ቋጭተው በነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ቅጣት ባስተናገደው በረከት ወልዴ ምትክ ክዋሜ ፍሪምፓንግ ተክቶት ገብቷል።


በሳምንቱ ከሚጠበቁ መርሐግብሮች መካከል አንዱ በሆነው የምሽቱ ጨዋታ በኮሪደሮች በኩል በተደረጉ ፈጣን እንቅስቃሴዎች በኋላ ሙከራዎችን በጊዜ አስመልክቶናል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች 4ኛው ደቂቃ ላይ ሞሰስ ኦዶ ከመሐል ክፍሉ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ለማግኘት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት የባህር ዳሩ ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶ ለማውጣት ሲዳዳ ያሬድ ባዬን ኳሷ ገጭታ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታለች። ፈረሰኞቹ ያገኙትን የማዕዘን ምት መጠቀም ያልቻሏትን ኳስ ከአንድ ደቂቃ በኋላ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኙት ባህር ዳሮች ፍሬው ሠለሞን በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ የአብስራ ተስፋዬ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ባህሩ ጋር መገናኘት ቢችልም የመታት ኳስ ግን የግቡን ቋሚ ብረት መትማ ተመልሳበታለች።

በጋለ ፉክክር ውስጥ ሆኖ በሽግግሮች እየታጀበ በቀጠለው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ከፍሬው እግር ስር በሚነሱ እና ቸርነት በጥልቀት ሰብሮ በመግባት በሚያደርጋቸው ተደጋጋሚ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ፈረሰኞቹ መነሻቸውን መሐል ላይ በማድረግ ሰንጣቂ ኳሶች ላይ ትኩረት አድርገው በይበልጥ ይጫወቱ እንጂ ቢኒያም ከተሰለፈበት የግራ የሜዳው ክፍል መነሻን አድርገው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት አደገኛ የሚባሉ አጋጣሚዎችን ያገኙ ነበር። ሜዳ ላይ ከእንቅስቃሴ መብዛቶች ውጪ ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ለመመልከት የደቂቃዎችን መሻገር መጠበቅ ተገደን ልክ ጨዋታው 29ኛ ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ባህርዳር ከተማዎች ፍራኦል ከቅጣት አሻምቶ ፍሬዘር በግንባር ገጭቶ ኳሷ የግቡን ቋሚ ታካ ወደ ውጪ መውጣት ብትችልም የዕለቱ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ወደ ማዕዘን ምትነት ቀይረዋት መሳይ አገኘሁ አጋጣሚዋን ተጠቅሞ ወደ ግብ ሲያሻማ ቸርነት ጉግሳ በግንባር ገጭቶ የቀድሞው ክለቡ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፎ ባህር ዳርን መሪ ማድረግ ችሏል።

ጎልን ካስተናገዱ በኋላ አቻ ለመሆን ጫናዎችን በሚፈጥር የመስመር አጨዋወት በይበልጥ ብልጫን መውሰድ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 33ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ በረጅሙ ከግራ በረጅሙ ያሻገራትን ኳስ ሞሰስ በግንባር ገጭቶ ፔፕ የተቆጣጠራትን እና 37ኛው ደቂቃ ላይም ከማዕዘን ቢኒያም አሻምቶ ናትናኤል በግንባር ገጭቶ መሳይ አገኘሁ ከግቡ መስመር ኳሷን ወደ ውጪ አውጥቷል። የአጋማሹ መባቻ ሲቃረብ ባህር ዳሮች ከቆሙ ኳሶች አልያም ደግሞ  በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ዕድሎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም በውሀ ሰማያዊዎቹ የ1ለ0 መሪነት ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከፍ ባለ ተነሳሽነት ባህርዳሮች በበኩላቸው ጥንቃቄ ላይ ባመዘኑ እንቅስቃሴዎች የቀጠሉበት ነበር። ሻል ብለው ቶሎ ቶሎ የሚገኙ ኳሶችን ተጠቅመው መዳረሻቸውን የተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ያደርጉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 53ኛው ደቂቃ ላይ ሔኖክ አዱኛ ከቀኝ ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በአግባቡ አለመቆጣጠሩን ተከትሎ ሞሰስ ኦዶ ያገኛትን መልካም ዕድል ሳይጠቀምባት ቀርቷል። እንደነበራቸው የጨዋታ አቀራረብ ብልጫን ወስደው ቢታዩም ከጎል ጋር ለመገናኘት የባህር ዳርን የመከላከል አጥር ለማለፍ የከበዳቸው ፈረሰኞቹ አከታትለው ዳግማዊ ፣ አላዛር እና ታምራትን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ቁጥራቸውን ከፍ ቢያደርጉም ዕድሎችን በመፍጠሩ ስሎች አልነበሩም።


ኳስን ለተጋጣሚያቸው በመተው በመልሶ ማጥቃት መጫወትን የመረጡት ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ቸርነት አመዝነው ተጨማሪ ጎልን ለማስቆጠር የሚሄዱበት ርቀት ግን  እንደ መጀመሪያው አጋማሽ አመርቂ ሊሆንላቸው አልቻለም። ሙከራዎች እምብዛም ባልነበሩም ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ 90ኛው ደቂቃ ላይ በፈረሰኞቹ በኩል በግራ ከቢኒያም ያገኘውን ኳስ ዳግማዊ ወደ ውስጥ ይዞ ገብቶ ከጠበበ አንግል ሞክሮ ፔፔ ሰይዶ ካዳነበት በኋላ ጨዋታው 90+4 ላይ ሲደርስ ሔኖክ ወደ ቀኝ የሰጠውን ኳስ አማኑኤል ተርፉ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኤርቦ በግንባር ገጭቶ የፔፔ ሰይዶ መረብ ላይ ኳሷን በማሳረፍ ፈረሰኞቹን በመጨረሻም ከሸንፈት ታድጎ 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ጨዋታው ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጠንካራ እና ከባድ ጨዋታ መሆኑን ጠቁመው በክፍተቶቻቸው ተጋጣሚያቸው ተጠቅሞ ጎል እንዳስቆጠረባቸው እና በመጨረሻ ደቂቃ ግን ተጫዋቾቻቸው ጥሩ ነገርን አድርገው ውጤት ይዘው መውጣት እንደቻሉ እና የአቻ ውጤቱም ተገቢ መሆኑንም ጭምር በንግግራቸው አውስተዋል። የባህርዳር ከተማ አቻቸው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው በጨዋታው ደስተኛ አለመሆናቸውን ጠቅሰው ሦስት ነጥብ ይገባናል ሲሉ በሂደቱ ግን ተጫዋቻቸው ያደረጉትን ጥረት በማመስገን አቻው እንደማይገባው ቡድናቸው ተጋጣሚያቸው ተጫውተው ነጥቡን እንዳልወሰዱ እና ጨዋታውም ስሜት እንደሚጎዳም ገልፀዋል።