መረጃዎች| 84ኛ የጨዋታ ቀን

በሁለቱ የሰንጠረዡ ፅንፍ በሚደረግ ፉክክር ወሳኝነት ያላቸው ሁለት የነገ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ

በወራጅ ቀጠናው ያሉ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ 10 ሰዓት ሲል ይጀምራል።

ከተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶች በኋላ ወላይታ ድቻን አሸንፈው በውድድር ዓመቱ ያስመዘገቡት ድል ሦስት ያደረሱት ወልቂጤ ከተማዎች በ13ኛ ደረጃ ከተቀመጠው መድን ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ችለዋል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ራተኞቹ በመጨረሻው ሳምንት ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ተስፋቸውን ያለመለመ ወሳኝ ድል ነበር ያስመዘገቡት ፤ ባለፉት ሳምንታት ያሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በውጤት ማጀብ ሳይችል ከቀረ በኋላ በተመስገን በጅሮንድ ግብ ሙሉ ነጥብ ያገኘው ቡድኑ ከድሉ ባሻገር ከተከታታይ ሽንፈቶች መራቁ የቡድኑ መሻሻል ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በውድድር ዓመቱ 21 ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ መስመር ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። በአማካይና በተከላካይ ክፍሉ ላይ የሚታይ ለውጥ ማምጣት የቻሉት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት የመሻሻል ሂደታቸውን በውጤት ለማጀብ የግብ ማስቆጠር ችግራቸውን መቅረፍ ግድ ይላቸዋል። ከዚህ በዘለለም የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን የማግኘት አኳኋናቸው ፍጥነቱን መጨመር እና ተጋጣሚ ሜዳ ላይ በተሻለ ጊዜ እና ብልጫ ባለው ቁጥር መገኘት ይኖርበታል።


በአስራ ሁለት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሻሸመኔ ከተማዎች ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች ለመላቀቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ። የነገው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ላለመውረድ በሚያደርጉት ጉዞ ያለው ወሳኝነት ትልቅ ቢሆንም ከተጋጣሚያቸው በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብለው ለተቀመጡት ሻሸመኔ ከተማዎች ይበልጥ ወሳኝ ነው። ይህ ተከትሎም ቡድኑ በሁሉም ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። በተለይም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማግኘት የተሳነው የፊት መስመር ከሌላው ጊዜ በተለየ ጥንካሬ ተላብሶ መቅረብ ግድ ይለዋል። የቡድኑ የፊት መስመር ጠንካራውን የባህር ዳር ከተማ ተከላካይ ክፍል በገጠመበት ጨዋታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቢያሳይም በጨዋታው የታየበትን የአፈፃፀምና የውሳኔ አሰጣጥ ችግር መፍታት አለበት።

ከቀደመ አቀራረባቸው እና ከተጋጣሚያቸው የአማካይ ክፍል ጥንካሬ በመንተራስ ቡድኑ በነገው ጨዋታ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ እንደማይሰጥ ይገመታል፤ ሆኖም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደውን የሠራተኞቹ የኋላ መስመር በተሻለ ለመፈተን የሚገኙትን ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም ዋነኛ ዕቅዱ መሆን ይኖርበታል።

ወልቂጤ ከተማዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በሻሸመኔ ከተማ በኩል ግን አራት ጨዋታዎች የተቀጣው ማይክል ኔልሰን በጨዋታው አይሰለፍም።

በመጀመሪያው ዚር ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ አንድ ለዜሮ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

መቻል ከ ኢትዮጵያ መድን

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እንዲሁም በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ተቀምጠው ነገ የሚገናኙት መቻልና እና ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት የነገ ፍልሚያ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይታመናል፡፡

በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብለው በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች መሪው ንግድ ባንክ ማሸነፉን ተከትሎ የተፈጠረውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ብርቱ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በመጨረሻው ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ የተለያየው ቡድኑ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቀጠል በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል አይኖርበትም። የነገው ጨዋታ በወረቀት ደረጃ ሲታይ ቀላል ቢመስልም በወራጅ ቀጠናው ለማንሠራራት ከሚገባው መድን የሚጠብቃቸው ፈተና ግን ቀላል አይሆንም። መቻሎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መረባቸውን አላስደፈሩም።
የመከላከል አደረጃጅቱም በቡድኑ ከታዩ በጎ ለውጦች አንዱ ነው፤ በነገው ዕለትም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ወደ ጥሩ ውህደት ከመጣው የመድን የፊት መስመር የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።

መቻሎች ምንም እንኳ ጠንካራ የኋላ መስመር መገንባት ቢችሉም የፊት መስመራቸው ስልነት ግን ደረት አያስነፋም። ቡድኑ ባለፉት ሦስት መርሐግብሮች በጨዋታ በአማካይ አንድ ግብ
አስቆጥሯል፤ ይህ ቁጥርም በጥራት ላቅ ያሉ የፊት መስመር ተጫዋቾች ላሉበት ቡድን ጥቂት መሆኑ አያጠያይቅም። የአፈፃፀም ችግራቸውን መፍታት ለዋንጫ በሚያደርጉት ፉክክር ያለው ፋይዳ ትልቅ ስለሆነም ለተጠቀሰው ክፍተት ከወዲሁ መፍትሔ ማበጀት ይኖርባቸዋል ።

ተከታያቸው ወልቂጤ ከተማ አንድ ጨዋታ እየቀረው የነጥብ ልዩነቱን ማጥበቡን ተከትሎ ወደ ወራጅ ቀጠናው የመግባት አደጋ ያንዣበበባቸው መድኖች ስጋት ካለው ቀጠና ለመውጣት ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል።

በሊጉ 28 ግቦች ያስተናገዱት መድኖች በዚህ ቁጥር የተሻሉ የሆኑት በግርጌ ካለው ሀምበርቾ እና ሀዋሳ ከተማ ብቻ ነው። ቡድኑ ምንም እንኳ ሲዳማ ቡናን በገጠመበት የመጨረሻው ጨዋታ መረቡን ባያስደፍርም ከዛ በፊት በተካሄዱት አምስት ጨዋታዎች ግን ስምንት ግቦች አስተናግዷል። ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች ማስቆጠሩን እንደ አንድ በጎ መሻሻል ማንሳት ተገቢ ቢሆንም የመከላከል ድክመታቸው በነገው ጨዋታ ሊፈትናቸው እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውን በውጤት ማጀብ ያልቻሉትና ከድል ጋር ከተራራቁ አስራ ሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት መድኖች ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ ቢሆንም በተከላካይ መስመራቸው ላይ ውስን ለውጦች ካደረጉ በብዙ ረገድ ያግዛቸዋል።


የቅርብ ሳምንታት ለውጦችን መሰረት በማድረግ ቡድኑ ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወትበት ዕድል ቢኖርም ከመርሐግብሩ ክብደትና ከጨዋታው ወሳኝነት አንፃር ግን በጋራ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት አደጋን ለመፍጠር የሚሞክርበት ዕድልም ይኖራል ተብሎ ይገመታል።

መቻሎች የግራ መስመር ተከላካዩን ዳዊት ማሞ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም። በኢትዮጵያ መድን በኩል ደግሞ አብዲሳ ጀማል አሁንም ቅጣት ላይ ሲገኝ ንጋቱ ገ/ሥላሴ ፣ ሰዒድ ሀሰንና አሚር ሙደሲር በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጣቸው ይሆናል።

ሁለቱ ክለቦች ነገ ለ15ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ መድኖች 17 ግቦችን በማስቆጠር ሰባት ጨዋታዎችን በድል ሲወጡ 6 ጊዜ መርታት የቻሉት መቻሎችም በተመሳሳይ 17 ግቦች አሏቸው። ከ14 ግንኙነቶቻቸው መካከል አንድ ጊዜ ብቻ ነጥብ በመጋራት ተለያይተዋል።