ሪፖርት | የወራጅ ቀጠናው ፍልሚያ ያለ አሸናፊ ተገባዷል

ከወራጅ ቀጠናው ለመሸሽ ማሸነፍ ግዴታ የሆነባቸውን ሁለት ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ ደካማ ፉክክር ተደርጎበት ያለ ጎል ተደምድሟል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ ተገናኝተው ሠራተኖቹ በ20ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን 1ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ መድን ተክሉ እና ራምኬል ሎክ ወጥተው ሙሉዓለም መስፍን እና ፉዓድ አብደላ ገብተዋል። ሻሸመኔዎች በአንጻሩ በባህር ዳር ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ያሬድ ዳዊት ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ስንታየሁ መንግሥቱ በጌታለም ማሙዬ ፣ አብዱልቃድር ናስር እና አብዱልከሪም ቃሲም ተተክተው ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ12ኛው እና 13ኛው ደቂቃ የመጀመሪያዎቹን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አስመልክቷል። በቅድሚያ ሻሸመኔዎች ያሬድ ዳዊት ሳይጠቀምበት በቀረው አጋጣሚ ወደ ግብ ሲደርሱ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ወልቂጤዎች ለተሰነዘረባቸው ጥቃት በቆመ ኳስ አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት ሞክረው ተመልሰዋል።

በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉት ወልቂጤ ከተማዎች አብዛኛውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከወደ ቀኝ ካደላ አቅጣጫ መሰንዘር ይዘዋል። በ22ኛው ደቂቃም ጋዲሳ መብራቴ በተጠቀሰው መስመር ሳጥኑ መግቢያ ላይ በመሆን የሞከረው ኳስ የግቡን የጎን መረብ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩቱ ደግሞ ተመስገን በጅሮንድ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ቡድኑን መሪ ሊያደርግ ነበር።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም የጠሩ የግብ ሙከራዎችን ማስመልከት ያልቻለው የሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኳስን ለመቆጣጠር በሚደረግ የመሐል ሜዳ ፍልሚያ ታጅቦ ተጀምሯል። በአጋማሹም ምንም እንኳን ዒላማውን የጠበቀ ባይሆንም በ54ኛው ደቂቃ በሻሸመኔዎች በኩል የግብ ሙከራ ተደርጓል።

ጨዋታው 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ አስደንጋጭ ጥቃት ተሰንዝሯል። በተጠቀሰው ደቂቃም ከቀኝ መስመር ጋዲሳ ለቡድኑ አምበል ሳምሶን ጥላሁን ያቀበለውን ኳስ ሳምሶን በጥሩ ሁኔታ ተጫዋች ካለፈ በኋላ መረቡ ላይ አሳረፈ ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው ኬን ሰይዲ ራሱን ለጉዳት ዳርጎ አምክኖበታል። በቀሪ ደቂቃዎች በወልቂጤ በኩል ተመስገን በሻሸመኔ በኩል ደግሞ እዮብ የፈጠሯቸው ዕድሎች ለግብነት የቀረቡ የነበረ ቢሆንም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። ደካማ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታውም ያለ ጎል ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ የወልቂጤ ከተማው አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በሁለቱም ቡድኖች በኩል ውጤቱ አስፈላጊ ስለነበረ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት እንደታየ ተናግረው ካላቸው የሦስት ነጥብ ብልጫ አንፃር ከተፎካካሪያቸው ባደረጉት ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘታቸው ጥሩ የሚባል እንደሆነ ጠቅሰዋል። የሻሸመኔው ምክትል አሠልጣኝ በቀለ ቡሎ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበረ አመላክተው ማጥቃት አስበው ወደ ሜዳ ቢገቡም ወደ አጥቂ መስመር ኳስ የሚያደርስ ተጫዋች ላይ መጠነኛ ክፍተት እንዳለ አስረድተዋል። አሠልጣኙ ጨምረውም ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ቡድናቸው በሊጉ እንደሚተርፍ ንግግር አድርገዋል።